ዜና ዜና

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መርማሪ ቦርድ ስራውን በይፋ ጀመረ::

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ከዛሬ ጀምሮ ስራውን በይፋ መጀመሩን አስታወቀ።

በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 93 ንዑስ አንቀጽ 6 ላይ እንደተመለከተው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀና በምክር ቤቱ ከጸደቀ በኋላ የሁከትና ብጥብጥ ተጠርጣሪዎችን አያያዝ የሚከታተልና የሚቆጣጠር መርማሪ ቦርድ ይቋቋማል።

በዚህ መሰረት የካቲት 23 ቀን 2010 ዓ.ም በጸደቀው የስድስት ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በህገ መንግስቱ በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት የኮማንድ ፖስቱን አፈጻጸም የሚከታተል መርማሪ ቦርድ ተቋቁሟል።

ቦርዱ ከተጣለበት ኃላፊነቶች መካከል በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦችን በአንድ ወር ጊዜ ማሳወቅ፣ በኮማንድ ፖስቱ የሚወሰዱ እርምጃዎች ኢ-ሰብዓዊ እንዳይሆኑ መከታተልና መቆጣጠር፣ በምርመራው ያረጋገጠውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እርምት እንዲወሰድ ለኮማንድ ፖስቱ ማሳወቅና የድርጊቱን ፈጻሚ አካላትም ህግ ፊት እንዲቀርቡ ማድረግ የሚሉ ይገኙበታል።

ሰባት አባላት ያሉት መርማሪ ቦርዱ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ በአዋጁ የተሰጠውን ስልጣንና ኃላፊነት ለመወጣት ከዛሬ ጀምሮ በይፋ ስራ ጀምሬያለሁ ብሏል።

የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ታደሰ ወርዶፋ ምርመራውን አዋጁ ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ እንደሚያከናውን ገልጸው፤ ቦርዱ ተዘዋውሮ በአካል ከመመልከት በተጨማሪ በህብረተሰቡ በሚደርሰው ጥቆማ ምርመራውን ያካሂዳል ነው ያሉት።

ነገር ግን ቦርዱ ብቻውን የተደራሽነት ችግር ስለሚኖርበት ኅብረተሰቡ ተገቢውን ጥቆማ እንዲያደርስ ጥሪ አቅርበዋል።

በኮማንድ ፖስቱ ቁጥጥር ስር ሆኖ በማንኛውም ሁኔታ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት የተፈጸመበት አካል በስልክ፣ በፋክስና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚገኘው የቦርዱ አድራሻ በአካል በመገኘት የተሟላ መረጃ የያዘ አቤቱታ ማቅረብ እንደሚችል አስታውቀዋል።

ባለፈው ዓመት በነበረው የአስቸኳይ አዋጅ ልምድ መወሰዱን የገለጹት ሰብሳቢው፤ ከአገሪቱ የቆዳ ስፋትና የሁከቱ ጥንካሬ አኳያ የነበረውን የተደራሽነት ችግር ለመቅረፍ የህግ ባለሙያዎችን ያካተተ የቴክኒክ ኮሚቴ አዋቅሮ የምርመራ ስራውን ያጠናክራል ብለዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ደንብና መመሪያዎች ከምክር ቤቱ ድረ ገጽ ማግኘት እንደሚቻልና ኅብረተሰቡ ተገቢው ግንዛቤ እንዲኖረው መርማሪ ቦርዱ ከሚዲያ ተቋማት ጋር በትስስር እንደሚሰራ ነው ያብራሩት።

በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 18 አና 25 የተከለከሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የደረሰበት ማንኛውም ግለሰብ እርምጃው በማን፣ መቼና የት እንደተወሰደበት የሚያሳይ የተማሏ መረጃ ማቅረብ እንደሚገባው ገልጸው፤ የአቤቱታ ማቅረቢያ አድራሻዎችንም ይፋ አድርገዋል።

በስልክ ቁጥር 0111- 54- 51- 89፣ በፋክስ ቁጥር 0111- 57- 39- 95 ወይም በመርማሪ ቦርዱ ቢሮ በአካል ማድረስ ይቻላል ነው ያሉት።

አዲስ አበባ የካቲት 29/2010 (ኢዜአ)