ዜና ዜና

የመከላከያ ሰራዊት አባላት ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ያሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል - የሰሜን እዝ ዋና አዛዥ

የመከላከያ ሰራዊት የተሰጠውን አገራዊ ተልእኮ ከመወጣት በተጨማሪ በህዳሴ ግድብ ላይ እያደረገ ያለውን ህዝባዊ ተሳትፎ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የሰሜን እዝ ዋና አዛዥ ገለፁ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ምስራቅ እዝ የነበረውን ቆይታ አጠናቆ ትናንት ወደ ሰሜን እዝ ገብቷል፡፡

የሰሜን እዝ ዋና አዛዥ ሌትናል ጀነራል ገብራት አየለ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት ሰራዊቱ የአገር ሰላምና ድንበር ከማስጠበቅ በተጨማሪ በተለያዩ የልማት ስራዎች የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

የሰራዊቱ አባላት ለዋንጫው ያላቸውን ክብርና አድናቆት ካደረጉት አቀባበል በተጨማሪ ቦንድ በመግዛት ህዝባዊ ወገንተኝነታቸው ዳግም በማስመስከር ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ዋንጫው ወደ እዙ መምጣቱ በሰራዊቱ ያለው አገራዊ ኃላፊነትና ህዝባዊ ወገንተኝነት እንዲጨምር የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በሁለት ቀናት ውስጥም የእዙ አባላት ከ250 ሺህ ብር በላይ በቦንድ ግዢ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

ዋጫውን ያስረከቡት የሰሜን ምስራቅ እዝ ምክትል አዛዥ ብርጋዴል ጄነራል ገብረ እግዚአብሄር በየነ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ህዝቦች የጋራ አሻራ የሆነውን የህዳሴ ግድቡ ዋንጫ በሰራዊቱ መካከል እንዲዘዋወር ማድረግ የሰራዊቱ አባላት የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያግዝ መሆኑን ገልፀዋል።

የመከላከያ ሰራዊታችን ህዝባዊነቱን በማጎልበት ለአገሪቱ ልማትና ቀጣይ እድገት መሰረት የሆነውን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ለማሳካት እያደረገ ያለውን ጥረት በዋንጫው ርክክብ ስነስርዓት ላይ ተገኝተው ያመሰገኑት ደግሞ በትግራይ ክልል የህዳሴ ግድብ ግንባታ አስተባባሪ አቶ ሃይለኪሮስ ጠዓመ ናቸው።

ሻምበል አልጀሊ አልማሕዲ በበኩላቸው የአገርን ዳር ድንበር ከማስከበር በተጨማሪ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል፡፡

የመቶ አለቃ ይብራር ዓሊ በበኩላቸው እንደገለፀው በሰራዊቱ መካከል ያለው ህዝባዊ ወገንተኝነት እየተጠናከረ መምጣቱ በህዳሴ ግድብ ላይ እያደረገ ያለው ተሳትፎ ማሳያ ነው፡፡

ምክትል መቶ አለቃ ሙሉ ጉዳ በበኩሉ ዋንጫው ወደ አካባቢው መምጣቱ ሰራዊቱ የሚያደርገውን ድጋፍ ይበልጥ እንዲነሳሳ የሚያደርገው ነው ብሏል።

ወታደር ሙሉነሽ ውብዬ የተባሉ የሰራዊቱ አባል በበኩላቸው ዋንጫው ማለት የአገራችን ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መገለጫ ነው። ማንኛውም ህዝብ ለዋንጫው የበኩሉን አስተዋፅኦ እያደረገ ስላለ እኛም እንደ ሰራዊት ከደመወዛችን በወር እየቆረጥን ነው ብለዋል።

የህዳሴ ግድቡ ዋንጫ ለአንድ ወር ያህል በሰሜን እዝ የተለያዩ ክፍሎች እየተዘዋወረ የሚቆይ ሲሆን የሰራዊቱ አባላትም የቦንድ ግዢ በማካሄድ ላይ መሆናቸው ለማወቅ ተችሏል።

የካቲት 27/62010 /ኢዜአ/