ዜና ዜና

እስራኤል በዘመናዊ ግብርና ዘርፍ ያላትን ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል እየሰራች መሆኑን አስታወቀች፡፡

እስራኤል በዘመናዊ ግብርና ዘርፍ ያላትን የካበተ ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል የጀመረችውን ሥራ አጠናክራ እንደምትቀጥል የአገሪቷ የእርሻና የገጠር ልማት ሚኒስትር ዩሪ አሪል ገለጹ።

የእስራኤል የእርሻና የገጠር ልማት ሚኒስትር ዩሪ አሪል በኢትዮጵያ የሦስት ቀናት ጉብኝታቸውን የጀመሩ ሲሆን በዛሬው ውሏቸው ከተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመወያየት ላይ ናቸው።

ሚኒስትሩ በቆይታቸው "እስራኤል ባለፉት ስልሳና ሰባ ዓመታት በመስኩ ያስመዘገበችው ውጤት ለኢትዮጵያም የግብርናው መስክ ቀጣይ እድገት እንደ አንድ ግብዓትነት ያገለግላል" በማለት ገልጸዋል።

እስካሁንም በእስራኤል ጥሩ ምርት መሰብሰብ የተቻለባቸው የአትክልትና የፍራፍሬ ዝርያዎች ለኢትዮጵያ በማስተዋወቅ በዘርፉ ያላትን ልምድ እያካፈለች ነው ያሉት።

ከእስራኤል በመምጣት የተዋወቀው የአቮካዶ ዝርያ ከኢትዮጵያ አየር ሁኔታ ጋር ተገናዝቦ፤ በከፍተኛ ጥራት ተመርቶ ለውጭ ገበያ በመቅረቡ አገሪቷ ተጠቃሚ መሆኗን ለአብነት ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል "በአሳ እርባታና በተለይም በኮምፒዩተር በታገዘ የመስኖ ሥራ ላይ ያሉ ልምዶችን እያካፈልን ነው" ያሉት ሚኒስትሩ፤ ይህ ስራ በቀጣይም ተጠናክሮ አንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ውኃን በአግባቡ አንዴት መጠቀም እንደሚቻልና ጨዋማ ውኃን አንዴት ማጣራት እንደሚቻልም ያላቸውን ልምድና ክህሎት ለማጋራት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በዘርፉ እስራኤል በርካታ የምርምር ባለሙያዎች ባለቤት መሆኗን ጠቁመው በዚህም ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ለማድረግ የሥልጠና መርኃ ግብር በማዘጋጀት በጋራ እንሰራለን ብለዋል።

ይህም በዘርፉ ያለውን የምርምር ውጤት ኢትዮጵያ እንድትቀምር በማድረግ የእውቀት ሽግግር ለማረጋገጥ ሁነኛ ዘዴ መሆኑን አስረድተዋል።

ጎን ለጎንም በሁለቱ አገራት መካከል የትብብር አድማሱን ለማስፋት የተደረሱ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን ገቢራዊ ለማድረግ ሥራዎችን እንሰራለን ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በእስራኤል ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ከእስራኤሉ አቻቸው ቤንጃሚን ኔትንያሁ ጋር በዘርፉ በትብብር ለመሥራት የደረሱበት ሥምምነት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንም አንስተዋል ሚኒስትሩ።

ከስምንት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት እስራኤል እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2014 የግብርናው ዘርፍ ለአጠቃላይ አገራዊ ምርት ያለው ድርሻ 3 ነጥብ 3 በመቶ ነበር።

ምንም እንኳን ዘርፉ ለበርካታ እስራኤላዊያን መተዳደሪያ ባይሆንም አገሪቱ እስከ 4 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስውን የውጭ ንግድ ገቢ እንደምታገኝበት ግን መረጃዎች ያሳያሉ።

አዲስ አበባ የካቲት 26/2010(ኢዜአ)