ዜና ዜና

የኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ እየተካሄደ ነው፡፡

የኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ሁለተኛው የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ በቴክኒካል ኮሚቴ ደረጃ ተጀምሯል።

በወቅቱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ እንደገለፁት፥ ሁለቱ ሃገራት በርካታ ዘመናትን የተሻገረ ጠንካራ ግንኙነት አላቸው።

ሁለቱ ሃገራት በንግድና ኢንቨስትመንት ያላቸው ትስስር እያደገ መሆኑን የጠቀሱት አምባሳደር ሱሌማን፥ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ የኢትዮጵያን ምርቶች በመግዛት ከቀዳሚዎቹ ተርታ እንደምትሰለፍ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት 10 ቢሊየን ብር ያስመዘገቡ 98 ያክል የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ኩባንያዎች፥ በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ ተጨማሪ የአረብ ኢሚሬትስ ባለሃብቶች በመሰረተ ልማት፣ በአረንጓዴ ልማት፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በኃይል ልማት፣ በባቡር ግንባታና ሌሎች ዘርፎች እንዲሰማሩ ድጋፍ እንደምታደርግም ጠቅሰዋል።

የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ የኢኮኖሚና የንግድ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞሃመድ ሸሪፍ በበኩላቸው፥ ሁለቱ ሃገራት ያላቸውን ታሪካዊ ግንኙነት ማሳደግ የሚችሉበት ሰፊ እድል አላቸው ብለዋል።

የሁለቱን ሃገራት ንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር የበለጠ ለማሳለጥም፥ በአየር ትራንስፖርት ተደራራቢ ቀረጥን ማስቀረት የሚያስችል ስምምነት እንዲፈረም የሃገራቸው ፍላጎት መሆኑን አንስተዋል።

በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ብሎም ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ ኢትዮጵያ ያላትን ገንቢ ሚናም አድንቀዋል።

የሁለቱ ሃገራት በቴክኒካል ኮሚቴ ደረጃ የሚያደርጉት ውይይት ነገም የሚቀጥል ሲሆን፥ ሁለተኛው የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ደግሞ ረቡዕ የየሃገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በተገኙበት እንደሚካሄድ ይጠበቃል።

መረጃው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ነው።

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 26 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ)