ዜና ዜና

ኢትዮጵያ ሠላምና መረጋጋትን ለማስፈን ያወጣችው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተገቢ ውሳኔ ነው…የጂቡቲ አምባሳደር

ኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጇ የቀጣናውን ብሎም የአህጉሩን ሠላምና መረጋጋት ከመጠበቅ አኳያ ወሳኝ መሆኑን በኢትዮጵያ የጂቡቲ አምባሳደር መሐመድ እድሪስ ፋራህ ገለጹ።

አምባሳደር ፋራህ የኢትዮጵያን ውሳኔ ምዕራባውያን ማክበር እንደሚገባቸውም ጨምረው ተናግረዋል።

አምባሳደሩ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ወደ አሳሳቢ ደረጃ ከመድረሱ በፊት ኢትዮጵያ ውሳኔውን ማሳለፏ ሰላም በሚፈልግ ማንኛውም አካል ዘንድ ተቀባይነት ያለው ነው።

አሁን በአገሪቷ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አኳያም የኢትዮጵያ መንግሥት ያወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አግባብነት ያለው ውሳኔ መሆኑን አምባሳደር ፋራህ ተናግረዋል።

እንደርሳቸው ገለጻ፤ ምዕራባውያን በተለይ በአፍሪካም ሆነ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ በስፋት ስለማያውቁ መቃወማቸው ስህተት ነው የሚል እምነት አላቸው።

"እኛ ጂቡቲ እንደ ጎረቤት አገርም እንደ እህትማማችነታችን በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ እንረዳለን" ብለዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የካቲት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማጽደቁ ይታወቃል።

ምክር ቤቱ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቀረበለትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈላጊነት ላይ በጥልቀት ከተወያየ በኋላ በምክር ቤቱ ከተገኙ 490 አባላት መካከል በ395 የድጋፍ ድምጽ፣ በ88 ተቃውሞ እንዲሁም በሰባት ድምጸ ተአቅቦ ማጽደቁ ይታወሳል።

የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስቱ አዋጁ በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎችና በተወሰኑ አካባቢዎች ተግባራዊ የሚደረጉ ክልከላዎችና ሌሎች ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ ይፋ ማድረጉም ይታወቃል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረትና የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ነች፡፡

አዲስ አበባ የካቲት 27/2010(ኢዜአ)