ዜና ዜና

በኢትዮጵያ የታዳሽ ሀይል ልማትን የሚያጎለብት ማዕቀፍ ይፋ ሆነ

በኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ልማትን ማጎልበት የሚያስችል ማዕቀፍ ይፋ ተደረገ።

የኢትዮጵያ-ዴንማርክ የጋራ የንፋስ ኃይል ልማት ፕሮጀክት ሴሚናር የሁለቱ አገራት የሃይል ልማት ባለሙያዎች እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

ማዕቀፉ ኢትዮጵያ እና ዴንማርክ የታዳሽ ኃይል ልማት ተባብረው መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ባለፈው ዓመት ማድረጋቸውን ተከትሎ የንፋስ ኃይል ልማትን ለማስፋፋትና የአገሪቷን የኃይል ስርጭት አገልግሎት ጥራት እንዲኖረው ለማድረግ የሚያስችል ነው።

በዚህ ወቅት የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያ በኃይል ዘርፉ ያላትን እምቅ አቅም ለመጠቀም በትኩረት እየሰራች ነው።

ማዕቀፉ የመንግስትና የግል ሽርክናን አንድ ላይ በማምጣት የኃይል ዘርፉን ማሳደግ የሚያስችል መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ በዘርፉ የላቀ ልምድ ካላቸው አገራት ተሞክሮ በመቀመር እንዴት መተግበር ይቻላል የሚለውን መመልከቱንም ገልፀዋል።

ለዚህም ባለፈው ጥር ወር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስትና የግል ሽርክና የህግ ማዕቀፍ ማጽደቁን ያስረዱት ሚኒስትሩ፤ በአገሪቷ ያለውን የኃይል፣ የትራንስፖርትና ሌሎች ተቋማት ለማሳደግ የሚጠቅም ነው ብለዋል።

በዘርፉ ያለውን የመሰረተ ልማት አቅርቦት ማሳደግ እንደሚገባና ይህም ከመንግስት ብቻ በሚገኝ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን የግሉ ዘርፍም የሚሰራበትንና የመነጨው ኃይል ወደ ቋት ገብቶ የሚሸጥበትን ሁኔታ ለመፍጠር እንደሆነ ነው ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ የተናገሩት።

በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ሜት ታይገሰን በበኩላቸው ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ልማት ዘርፍ ያልተነካ ትልቅ አቅም አላት ብለዋል።

ዴንማርክ በዘርፉ ያላትን ልምድና አቅም በመጠቀም አገሪቷ የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኛ ዘርፎችን ለማስፋት የምታደርገውን ጥረት ትደግፋለች ብለዋል።

ድጋፉም አገሪቷ እያስመዘገበች ያለውን ፈጣን እድገት ለማስቀጠልና የኃይል ልማቱን ለማፋጠን ይረዳታል ያሉት አምባሳደሯ፤ ኢትዮጵያ በ2025 ያለመችውን ለአረንጓዴ ልማት የማይበገር ኢኮኖሚ የመገንባትና መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ እንደሚያግዛት ጠቁመዋል።

ዴንማርክ በኢትዮጵያ ለዘርፉ ልማት የሚውል የ4 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ባለፈው ዓመት ማድረጓ የሚታወስ ሲሆን ማዕቀፉ በኃይል ዘርፍ ተቋማዊ መዋቅሯን ለማጎልበት ይረዳል ተብሎም ይጠበቃል።
ኢዜአ፣ አዲስ አበባ የካቲት 26/2010