ዜና ዜና

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ የተደነገጉ ክልከላዎችና የሚወሰዱ እርምጃዎች ዛሬ ይፋ ተደርገዋል ፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ አቶ ጌታቸው አምባዪ ይህንን አስመልክቶ ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ጠቅላይ አቃቢ ህጉ እንዳብራሩት ዋና አላማው ሶስት ጉዳዮችን ለማስገንዘብ መሆኑን በመግለጽ፡-

1. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተመለከተ በህብረተሰቡ ግልፅነት እንዲፈጠር ለማድረግ ፣

2. በሁከትና ብጥብጥ ኃይል ተሰብከውና ተታለው እንዳይገቡ ለማድረግ እንዲሁም

3. በሁከትና ብጥብጥ ሀይል እየተሳተፉ የሚገኙ አካላት ካሉም ከድርጊታቸው እዲታቀቡ ለማድረግ እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡

በዚህም መሰረት በአዋጁ የተደነገጉ ክልከላዎችን አስመልክቶ የተላለፉት መመሪያዎች በሁለት አይነት የተከፈለ ሲሆን ፥

በመላው ሀገሪቱ የሚተገበሩ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈፃሚ ኮማንድ ፖስቱ በሚለያቸው ቦታዎች ተግባራዊ የሚደረጉ ክልከላዎችን የያዘ መሆኑን የጠቅላይ አቃቢ ህጉ በዝርዝር አብራርተዋል።

በመላው ሀገሪቱ የሚተገበሩ ክልከላዎችን በተመለከተ
1. ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥሉ ተግባራትን መፈፀም፥

በመመሪያው መሰረት ማንኛውም ሰው በሀይል፣ በዛቻ እና በየትኛውም መልኩ ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን የሚጥስ ተግባር መፈፀም የለበትም፤ የጦር መሳሪያ ይዞ ሁከት መፍጠር እና የእርስ በእርስ ግጭት እንዲኖር ማድረግም የተከለከለ መሆኑን፣

2. የህዝቦችን አንድነትና መቻቻል የሚሸረሽር ተግባር ብሄርን፣ሀይማኖትን ጾታን መሰረት በማድረግ ጥቃት መፈጸም የተከለከለ መሆኑን፣

3. ከአሸባሪ ድርጅቶችና ግለሰቦች ጋር ግንኙነት ማድረግ እና መደገፍ የተከለከለ መሆኑን ፣

4. የትራንስፖርት እንስቃሴን ማወክ ወይም ማስተጓጎል የተከለከለ መሆኑን፣

5. የህዝብ አገልግሎት ማስተጓጎል፣ ማቋረጥ እና መዝጋት

6. በመሰረት ልማትና በተለያዩ ተቋማት ጉዳት ማድረስ የተከለከለ መሆኑን ፣

7. በህግ አስከባሪ አካላት ላይ ጥቃት ማድረስ ወይም ጥቃት ለማድረስ ሙከራ ማድረግ የተከለከለ መሆኑን፣

8. ያልተፈቀደ ሰልፍ እና የአደባባይ ስብሰባ ማድረግ የተከለከለ መሆኑን ፣

.9. በትምህርት ተቋማት አድማ ማድረግና የመማር ማስተማሩን ሂደት ማስተጓጎል የተከለከለ መሆኑን፣

10. በስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች አድማ ማድረግ

11. በድብቅም ሆነ ይፋዊ የሆነ ሁከትና ብጥብጥ የሚያነሳሳ ቅስቀሳ እና ግንኙነት መፍጠር የተከለከለ መሆኑን፣

12. የመሰረታዊ ሸቀጦችን ዝውውር ማስተጓጎል፣ (ለህብረተሰቡ እንዳይደርሱ ማድረግ)፣

13 . ባህላዊ፣ ህዝባዊ፣ ሀይማኖታዊ እና ብሄራዊ በዓላትን ማወክና ማደናቀፍ የተከለከለ መሆኑን ፣

14. በገበያ፣ ሀይማኖታዊ ተቋማት፣ በዓላት እና ሕዝብ በተሰበሰበበት ስፍራ የጦር መሳሪያ ይዞ መግባትም ሆነ መንቀሳቀስ የተከለከለ መሆኑን ፣

15. የህዝብን ሰላምና ፀጥታ ለማደፍረስ የገንዘብ፣ የቁሳቁስ እና ሌሎች ድጋፎችን ማድረግም የማይፈቀድ መሆኑን፣

16. ፈቃድ ከተሰጠው የመሳሪያ (የትጥቅ) ባለቤት ውጭ ለ3ኛ አካል ወይም ለሌላ ሰው አሳልፎ መስጠት የተከለከለ መሆኑን፣

17. የፌዴራልም ሆነ የክልል አካል ከኮማንድ ፖስቱ ትዕዛዝ ውጭ በፀጥታ ጉዳይ ላይ መግለጫ መስጠት የማይችል መሆኑን ፣

18. አዋጁን መሰረት አድርገው የወጡ ህጎችንና አዋጆችንና መመሪያዎችን መቃወም የተከለከለ መሆኑን ህብረተሰቡ መገንዘብ እንዳለበትም ተገልጹአል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈጻፀም ተከትለው የወጡ ደንቦችና መመሪያዎችን አስመልክተው የሚከለክሉ ድንጋጌዎች የተገለጹ ሲሆን እነዚህ ክልከላዎች በመላ ሀገሪቱ የሚተገበሩ ክልከላዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም፡-

በተወሰኑ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚተገበሩ ክልከላዎችም ይፋ የተደረጉ ሲሆን እነዚህም ፡-

1. የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስን በተመለከተ፡-

የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስት ክልከላ በሚያደርጋቸው ባልተፈቀደባቸው ስፍራዎች የትኛውንም የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ የማይፈቀድ መሆኑን፣

2. የሰዓት እላፊ ገደብ በተመለከተ፡-የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስት ይፋ በሚያደርጋቸው ስፍራዎች የሰዓት እላፊ ገደብ ያስቀምጣል፡፡

በትላልቅ ፋብሪካዎች፣ በኢንዱስትሪ ማዕከላት በሰፋፊ የእርሻ ልማት ቦታዎች፣ የሰዓት እላፊ የሚጣልባቸው ስፍራዎች ናቸው።

3. የዜጎችን ደህንነት በተመለከተ፡-የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል ዜጎችን በአንድ በተወሰነ ስፍራ ማቆየት፤ ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላ ማዘዋወር

4. ለአካባቢ ስጋት ሲባል ወደ ተዘጋ መንገድ መግባትን መከልከልን፣

3 የመተግበር እና መረጃ የመስጠት በተመለከተ

3. 1 የቤትና የተሽከርካሪ አከራዮችን

የተከራይን አካል ማንነት መዝግቦ በግልፅ መያዝ፣ በፅሁፍ የሰፈረውን መረጃ በ24 ሰዓት ውስጥ በአካባቢው ለሚገኝ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ማሳወቅ፣ ተከራዩ የውጭ ሀገር ዜጋ ከሆነ የተከራዩን ፓስፖርት እና የኪራይ ውል ለፖሊስ የማቅረብ ግዴታ አለባቸው።

3.2 መረጃ የመስጠት ግዴታማንኛውም ተቋም(ግለሰብ) በተጠየቀበት ጊዜ ለህግ አስከባሪ አካል መረጃ የመስጠት ግዴታ አለበት።

3.3 ማንኛውም ሰው የኮማንድ ፖስቱን ውሳኔ የማክበር እና የመተግበር ግዴታ አለበት።

4 የሚወሰዱ እርምጃዎችን በተመለከተ
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፎ መገኘት እርምጃዎችን የሚያስወስድ መሆኑን።

የሚወሰዱ እምጃዎችም ፦

ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ በቁጥጥር ስር ማዋል፣
በቁጥጥር ስር የሚውሉ ሰዎችን ኮማንድ ፖስቱ በወሰነው ቦታ እንዲቆዩ ይደረጋል፤

ማንኛውም ስፍራ እና አካል ላይ በማንኛውም ሰዓት ብርበራ ማድረግ፤
የተዘረፉ ንብረቶችን አጣርቶ ለባለቤቶቹ እንዲመለሱ የማድረግ ፤
በትምህርት ተቋማት ብጥብጥ የሚፈጥሩ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ፤ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ
አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማዘዝ።

5. የሀይል አጠቃቀም

የህግ አስከባሪ አካላት እና የጥበቃ ሀይሎች የራሳቸውን ደህንነት መጠበቅ ይችላሉ።

የዜጎችን ደህንነት እና የኢንቨስትመንት ተቋማትን የመጠበቅ ግዴታ አለባቸው።

ህብረተሰቡ ሊያደርገው ስለሚገባው ጥንቃቄ በተመለከተ

ብርበራ ፍተሻ በሚካሄድበት ወቅት ብርበራ የሚያደርጉትን ኮማንድ ፖስት ማንነት የማወቅ መታወቂያዎችን በማየት፣

ከአካባቢ ነዋሪ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸውን
የአካባቢው የማህበረሰብ ፖሊስ (ኮሙዪኒቲንግ ፖሊስ) መኖሩን ማረጋገጥ ይገባዋል፡፡

የካቲት 26/2010(የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት )