ዜና ዜና

በትግራይ የሚካሄደው አፈርና ውሀ ጥበቃ ስራዎች መጪውን ትውልድ ታሳቢ ያደረጉ መሆኑ ተገለጸ

በትግራይ ክልል በየዓመቱ የሚካሄዱት   የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራዎች መጪውን ትውልድ በልማት የተሻለ አካባቢ ለማስረከብ ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ተገለጸ፡፡

በክልሉ በአርሶ አደሩ ነፃ የጉልበት አስተዋጽኦ እየተከናወነ ባለው የአፈርን ውሃ ጥበቃ ስራ 100ሺህ ሄክታር የተጎዳ መሬት እንደሚለማ የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አመልክቷል፡፡

በስራው እየተሳተፉ ካሉት አርሶ አደሮች መካከል በአጽቢ ወንበርታ ወረዳ የሓየሎም ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሀጎስ ገብረመድህን እንዳሉት ከ1987ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን የአፈርና ውሀ ጥብቃ ስራ እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡

በዚህም በጎርፍ ተሸርሽሮ የነበረው አካባቢ በደን እየለበሰ አሁን ንጹህ አየር ከማግኘታቸው በተጨማሪ በመስኖ የሚለማ መሬትም እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"አሁን የምንሰራቸው የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራዎች ቀጣዩ ትውልድ ተጠቃሚና የተሻለ ህይወት እንዲኖረው ከማሰብ ነው" ብለዋል አርሶ አደር ሀጎስ፡፡

"ሴቶች ከወንዶች እኩል በስራው በመሳተፍ ልጅ አዝለን ድንጋር እየፈለጥን በአፈርና ውሀ ጥበቃ እየተሳተፍን  ነው " ያሉት ደግሞ ሴት አርሶ አደር ወይዘሮ  ለምለም ካህሳይ ናቸው፡፡

ወይዘሮዋ እንዳሉት ወላጆቻችን በአካባቢ ጥበቃ ላይ የተሻለ ስራ ባለማከናወናቸው አካባቢያቸው ተራቁቶ ቆይቷል፡፡

የቀበሌው አርሶ አደር ካሕሱ ተስፋዬ በበኩላቸው "የአካባቢ ጥበቃ ስራ ያለማቋረጥ ለዓመታት በመሰራቱ የእርሻ መሬታቸው በጎርፍ ከመወሰድ ተርፈዋል " ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በጎርፍ ተቦርቡሮ ከጥቅም ውጭ ሆኖ የነበረውን  ቦታ መልሶ እንዲያገግም በማድረጋቸው በአቅራቢያቸው ለእንስሳትና ለሰው መጠጥ የሚሆን ውሀ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

በአለም አቀፍ የእጽዋት ምርምር ማዕከል  የገርገራ ተፋሰስ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ገብረህይወት ሀይለማሪያም  በበኩላቸው የአከባቢ ጥበቃ ስራዎችን ወደ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሸጋገር በምርምር የተደገፈ ስራ አርሶ አደሩን እያገዙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

አካባቢው ለቋሚ አትክልት አመቺ በመሆኑ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በአጽቢ ወንበርታ ወረዳ የመስኖ ባለሙያ አቶ ጽዱቅ ተስፋዬ በበኩላቸው ለዓመታት በተካሄደው የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ ወራጅ ወንዞችና የጉድጓድ ውሀ በቀላሉ በመገኘቱ ከ290 ሄክታር መሬት በመስኖ ማልማት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በተለይም ከአርሶ አደሩ ጉልበት በላይ የሆኑ ስራዎች በገንዘብ ድጋፍ በማድረግ አለም አቀፍ የእጽዋት ምርምር ማዕከል ድጋፍ እየሰጠ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት በተፋሰሱ የተካሄዱ የክትር ስራዎች 36 ሄክታር የእርሻ መሬት ከጎርፍ ማዳን መቻሉን አቶ ጽዱቅ ጠቅሰዋል፡፡

በትግራይ በአርሶ አደሩ ነፃ የጉልበት አስተዋጽኦ የሚካሄደውን ይሄው ስራ 100ሺህ ሄክታር መሬት ለመሸፈን ከየካቲት 5/2010ዓ.ም ጀምሮ ለሀያ ቀናት የሚቆይ በሁሉም ወረዳዎች መቀጠሉን የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አመልክቷል፡፡

የካቲት 17/2010/ኢዜአ