ዜና ዜና

የዩኒቨርስቲ ኢንዱስቱሪ ትስስር ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

የዩኒቨርስቲና ኢንዱስትሪ ትስስር ላይ ያለውን ችግር በመዳሰስ የመፍትሄ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ  የምክክር መድረክ  ትናንት በመቀሌ ዩኒቨርስቲ ተካሂዷል፡፡

በዚሁ ወቅት የዩኒቨርስቲው የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝደንት ዶክተር አብደርቃድር ከድር እንዳሉት ተቋማቸው  በየዓመቱ ብዛት ያላቸው  ተማሪዎችን የተግባር ትምህርት እንዲያገኙ ወደ ኢንዱስትሪዎች ይልካል፡፡

ተማሪዎች ወደ ኢንዱስትሪ ለተግባር ትምህርት ሲልኩ በንድፈ ሀሳብ የሚያውቁትን በተግባር በማበልጸግ ብቃት ያላቸው ዜጎች ለማፍራት ታሳቢ በማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ወደ  ኢንዱስትሪ የሚላኩ ተማሪዎች የማብቃት ኃላፊነቱ  የዩኒቨርስቲው ብቻ ሳይሆን በትምህርት በልጽገው የመውጣትና አለመውጣት ጥቅሙና ጉዳቱ የጋራችን  ነው "ብለዋል፡፡

ዶክተር አብደርቃድር እንዳመለከቱት በዩኒቨርስቲና በኢንዱስትሪ መካከል ያለውን ግንኝነት አንዱ ከሌላው ጋር ያለውን የእውቀት  ክፍተት በማስተካከል  ረገድ ተመጋጋቢ ሊሆኑ ይገባል፡፡

ከኢንዱስትሪዎች መካከል የትግራይ ባዮ ቴክኖሎጂ ተወካይ አቶ አሰፋ ብርሀኑ በበኩላቸው ለተግባር ትምህርት የሚመደቡ በርካታ ተማሪዎች እንደሚቀበሉ ተናግረዋል፡፡

ባዮ ቴክኖሎጂው ከተማሪዎቹ በምርምር ሊያገኘው  የሚችል በርካታ ቁም ነገሮች ቢኖርም  እስከ አሁን ግን ተጠቃሚ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

"በተለይም  ከውጭ የሚያስመጣውን የተመረጠ አፈር ከዩኒቨርስቲው የኬሚስትሪ ተማሪዎች በምርምርና ጥናት ማግኘት ሲገባው እስከ አሁን ምንም ግብአት ሊያገኝ አልቻለም "ብለዋል፡፡

ከስድስት ዩኒቨርስቲዎች የተግባር ትምህርት ተማሪዎች በየዓመቱ እንደሚቀበሉ የተናገሩት ደግሞ በመቐለ  የሞሃ ለስላሳ አክስዮን ማህበር ፋብሪካ የሰው ሀብት መምሪያ ኃላፊ አቶ በሪሁ ገብረማሪያም ናቸው፡፡

" ከኢንጂነሪንግና ከምግብ ሳይንስ በርካታ ተማሪዎች የሚቀበሉ ቢሆንም በዩኒቨርስቲዎች በኩል ተማሪዎቻቸውን የመከታተልና ድጋፍ የማድረግ ችግር አለባቸው" ብለዋል፡፡

በዩኒቨርቲውና በኢንዱስትሪው መካከል  ችግሩን የሚፈታ ስርአት መዘርጋት  እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

በዩኒቨርስቲው  ኢንዱስትሪና ማህበረሰብ ትስስር ዳይሬክተር ዶክተር አለምጸሀይ ጸጋይ " ለተግባር ትምህርት ወደ ኢንዱስትሪ ከሚላኩ ተማሪዎች 65 በመቶ ክትትል  ያንሳችዋል "ብለዋል፡፡

ትስስሩን  ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በኢንዱስትሪ ባለቤቶች የሚሰጥ የተግባር ትምህርት ውጤት የዩኒቨርስቲው አስተማሪዎች ከሚሰጡት ውጤት ተቀራራቢ ወይም የተሻለ የምዘና ስርዓት እንዲኖረው ለማስቻል ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተመካከሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የዩኒቨርስቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝደንት ፕሮፌሰር ፈትየን አባይ በበኩላቸው " ለተግባር ትምህርት ተማሪዎችን ተቀብለው የሚያስተናግዱ ተቋማት ተጠቃሚ የሚሆንበት ስርዓት መዘርጋት አለበት "ብለዋል፡፡

ኢንዱስትሪዎቹ  ለተማሪዎች የሚያወጡት ወጪ የሚሸፍን የታክስ ቅነሳ የሚያገኙበት አልያም በምርምር ስራዎች ቅድሚያ ተጠቃሚ የሚሆንበት ሁኔታ ለመፍጠር  ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መስራት አለባቸው ብለዋል፡፡

የካቲት 16/2010/ኢዜአ