ዜና ዜና

የጣና ሃይቅን ህልውና የሚፈታተኑ ችግሮችን በመፍታት የሃይቁን ዘላቂ ደህንነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ተገለጸ

የጣናን ዘላቂ ደህንነት ለማረጋገጥ እምቦጭ አረምን ከማስወገድ ባሻገር የሃይቁን ህልውና የሚፈታተኑ ሌሎች ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ የአማራ ክልል አካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ አሁን ላይ ሃይቁን የወረውን እምቦጭ አረምን ከማስወገድ ባሻገር፥ ለሃይቁ ስጋት የሆኑ ጉዳዮችን መቅረፍ እንደሚገባ ገልጿል።

የባስልጣኑ ዋና ዳሬክተር ዶክተር በላይነህ አየለ፥ በሃይቁ ዙሪያ የሚከናወኑ የግብርናና ሌሎች የልማት ስራዎች ሀይቁ ላይ ተፅዕኖ እንዳያደርሱ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም በሃይቁ ዙሪያ የሚገኙ ከተሞችን የቆሻሻ አወጋገድ ማስተካከል፣ የአፈር ብክለትን መከላከል፣ የብዝሀ ህይወት ጥበቃ ስራዎችን ማጠናከርም ለሃይቁ ህልውና አስፈላጊ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ለዚህ የሚያግዝ የተቀናጀ ስትራቴጂክ እቅድ እየተዘጋጀ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፥ በሃይቁ ላይ የተጋረጡ ችግሮችን ለመፍታት የክልሉ መንግስት የጣና ሀይቅና አካባቢው ደህንነት ፈንድ ማቋቋሙን ገልጸዋል።

በፈንዱ አማካኝነትም እስካሁን 3 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ተሰብስቧል ብለዋል፤ ህብረተሰቡ ለሃይቁ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

ባለፈው መስከረም ወር በተጀመረው የዚህ አመት አረም የማስወገድ ዘመቻ፥ በተለይም በደንቢያና የደቡብ ጎንደር የጣና አዋሳኝ ወረዳዎች በአረም የተወረረውን የሃይቁን ክፍል ከስጋት መታደግ መቻሉን አንስተዋል።

ይሁን እንጅ በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ሀይቁ በቦታው ካለው ጥልቀት አኳያ በሰው ሀይል ለማስወገድ አስቸጋሪ መሆኑን ጠቅሰዋል፡

በጣና ሃይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም ለማስወገድ የሚያስችል ዘመናዊ ማሽን በአማጋ ኃ/የተ/የግ/ ማህበር ተገዝቶ ወደ ሃገር ውስጥ የገባ ሲሆን፥ ከነገ ጀምሮ ከቻይና በመጣ ባለሙያ ማሽኑን የመገጣጠም ስራ ይከናወናል።

ከዚህ ባለፈም ማሽኑን የሚያንቀሳቅሱ ባለሙያዎችን በስድስት ቀናት ውስጥ በማሰልጠን፥ ማሽኑ በቀናት ውስጥ ወደ ስራ እንደሚገባ ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

አሁን ላይም ከሃይቁ የሚወጣው አረም የሚወገድበትን ወደብ በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ሸሀ ጎመንጌ በተባለ ቦታ ላይ ለመገንባት የቦታ መረጣ ስራና ወደ ወደቡ የሚያደርስ መንገድ ግንባታ መከናወኑም ተገልጿል።

ሃገር ውስጥ ከገባው ማሽን በተጨማሪም "አለም አቀፍ ጥምረት ለጣና መልሶ ማገገም" በተባለ የበጎ አድራጊዎች ጥምረት የተገዛውን ሁለተኛ ማሽን ከመጋቢት ወር ጀምሮ ወደ ሃገር ውስጥ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ ነው ተብሏል።

እንቦጭ አረምን በዘመናዊ ማሽን ለማስወገድ ከሚደረገው ጥረት ባሻገር አሁንም በህብረተሰቡ ጉልበት አረሙን የማስወገድ ንቅናቄ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው የተባለው።

37 ደሴቶችን አቅፎ የያዘውና የአባይ ወንዝ መነሻ የሆነው ጣና ሀይቅ፥ ለአለም ስነ-ምህዳር ብዝሀነት ባለው አስተዋጽኦና በውስጡ በያዛቸው ሀብቶች የአለም ጥብቅ ቦታ ሆኖ መመዝገቡ ይታወሳል፡፡

 የካቲት 17 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ)