ዜና ዜና

የባቦጋያ ማሪታይምና ሎጅስቲክስ አካዳሚ በማሪን ቴክኒክና ሙያ በአምስት የትምህርት ክፍሎች ከደረጃ አንድ እስከ አምስት ስልጠናዎችን ለመስጠት ዝግጅቱን እያጠናቀቀ ነው ተባለ፡፡

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት እያከናወናቸው ካሉት ተግባራት መካከል ከፊሎቹን ትናንት ለህዝብ ግንኙነትና የሚዲያ አካላት አስጎብኝቷል፡፡

የጉብኝቱ አንዱ አካል የሆነውና በኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የተቋቋመው የባቦጋያ ማሪታይምና ሎጂስቲክስ አካዳሚ የአጫጭር የማሪን የመሰረታዊ ደህንነትና የባህረኝነት ሙያ ለድርጅቱ መርከበኞችና በተለያዩ የውጭ ሀገር መርከቦች ለመስራት ፍላጎት ያላቸውን የግል ሰልጣኞች ለማሰልጠን ተብሎ የተቋቋመ ነው፡፡

የአካዳሚው የስልጠናና ስርአተ ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ግርማ ተሾመ እንደገለፁት ተቋሙ በግል ደህንነትና ማህበራዊ ሀላፊነት፣ በእሳት አደጋ መከላከልና መቋቋም፣ በመጀመሪያ ህክምና እርዳታ አሰጣጥና ሌሎች ዘርፎች ስልጠና ይሰጣል፡፡

በባቦጋያ ማሪታይምና ሎጂስቲክ አካዳሚ አካባቢ ላሉ ሪዞርቶችና ሆቴሎች የእሳት አደጋ መከላከልና መቋቋም እንዲሁም የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ አሰጣጥ ስልጠናዎችን የሰጠ ሲሆን የጀልባ ማስጎብኘት ላይ ለተሰማሩ ወጣቶችና አሳ አስጋሪዎች ደግሞ የማሪን ውሀ ብክለት መከላከል፣ የጀልባ ምዝገባና ደህንነት እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃ ስልጠናዎችን በመስጠት አካዳሚው ማህበራዊ ሀላፊነቱን እየተወጣ ነው ሲሉ አቶ ግርማ ተናግለዋል፡፡

አካዳሚው እስከአሁን 200 ለሚሆኑ በውጭ ሀገር መርከቦች ለሚሰሩ ሰራተኞች አጫጭር ስልጠና የሰጠ ሲሆን ከተመሰረተበት 2002 ዓ.ም ጀምሮ 4500 ለሚሆኑ ሰልጣኞች በተለያዩ ዘርፎች ስልጠና መስጠቱ ተነግሯል፡፡

በቀጣይም አካዳሚው 44 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ባስገነባው አዲስ ህንፃ አስፈላጊውን ግብዓት በማሟላት ላይ ሲሆን በቅርቡ በማሪን ቴክኒክና ሙያ በአምስት የትምህርት ክፍሎች ከደረጃ አንድ እስከ አምስት ስልጠናዎችን ለመስጠት ዝግጅቱን ማጠናቀቁ በጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል፡፡

አካዳሚውን በምስራቅ አፍሪካ ብቸኛው የማሪታይም ዩኒቨርሲቲ ለማድረግ ከኦሮሚያ ክልል መንግስት 10 ሺህ ስ.ሜትር መሬት ለመረከብ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ተደርሷል ተብሏል፡፡

የባቦጋያ ማሪታይምና ሎጅስቲክስ አካዳሚ ከአዲስ አበባ በስተምስራቅ አቅጣጫ በ 47 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡

የካቲት 17/2010 /የኢፌዲሪ መ/ኮ/ጉ/ፅ/በት/