ዜና ዜና

የአድዋ ድል ኢትዮጵያውያን አርበኞች ለዛሬው ማንነታችን መሰረት የጣሉበት ታሪካዊ ድል ነው - የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር

የአድዋ ድል ጀግኖች ኢትዮጵያውያን አርበኞች በአንድነት ተፋልመው ለዛሬው ማንነታችን መሰረት የጣሉበት ታላቅ ታሪካዊ ድል መሆኑን የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ርስቱ ይርዳው ተናገሩ።

ኢትዮጵያውያን ለወረራ የመጣውን የጣሊያን ጦር በአድዋ ሰንሰላታማ ተራሮች ድል የነሱበት የአድዋ ድል፥ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የቅኝ ግዛት ቀንበርን ለሚፋለሙ የነፃነት ታጋዮች አዲስ የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀ ነው።

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ርስቱ ይርዳው ከጣቢያችን ጋር በነበራቸው ቆይታ የአድዋ ድል ከኢትዮጵያ አልፎ በአለም ታሪክ የራሱን አሻራ ማስቀመጡን ይናገራሉ።

ሚኒስትሩ የአድዋ ድል እነዚያ ጀግኖች አርበኞች በጥቁር ህዝቦች ታሪክ ውስጥ የተፃፈውን ደማቅ ታሪክ መክተባቸው ለዛሬው ማንነታችን መሰረት ነው ይላሉ።

እርሳቸው በዛሬይቱ ኢትዮጵያ በአድዋ ተራሮች የተፈፀመው ገድል የኢትዮጵያውያን የአንድነት መገለጫ ሆኖ የሚያበራ መሆኑንም ይናገራሉ።

ጡረተኛው ዲፕሎማት አቶ ፍስሃ አፈወርቅ በበኩላቸው የአድዋ ድል፥ ኢትዮጵያውያን ከጫፍ ጫፍ ተነስተው ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለአለም ጭቁን ህዝብ ተምሳሌት የሆነ ገድል የፈፀሙበት ነው ይላሉ።

የታሪክ ተመራማሪው ዲያቆን ዳንኤል ክብረትም በዚህ ሀሳብ ይስማማሉ፤

የዛሬው ትውልድ አንገቱን ቀና አድርጎ እንዲጓዝ ያስቻለው የትናንቱ የጀግኖች አርበኞች በአንድነት መንፈስ የሰሩት ታሪክ ውጤት መሆኑን በመጥቀስ።

ይሁን እንጅ ለዛሬው ማንነታችን መሰረት ከመሆን አልፎ ለአለም ጭቁን ህዝቦች የነፃነት ጥያቄ እንዲያንሰራራ መልካም አብነት የሆነው የአድዋ ድል ከታሪካዊ ፋይዳው አኳያ የሚገባውን ትኩረት እንዳልተሰጠውም ይገልጻሉ።

ምሁራኑ ለዚህ ድል ከአሁኑ የተሻለ ሰፊ ትኩረት መሰጠት እንዳለበትም ነው የሚናገሩት።

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ርስቱ ይርዳው ደግሞ ከአድዋ ድል የዛሬዎቹ ወጣቶች የሚማሩት ትልቅ ቁም ነገር እንዳለ ነው የሚገልጹት።

ወጣቶች ዛሬም እንደ አያቶቻቸው የኢትዮጵያን አንድነት በሚፈታተኑ ነገሮች ላይ የጋራ አቋም መያዝ አለባቸው ነው የሚሉት።

ምሁራኑ ለአድዋ ድል እና መሰል ሀገራዊ አንድነትን ለሚያጠናክሩ በዓላት ልዩ ትኩረት መስጠት ጠቀሜታው በርካታ ነው ይላሉ፤ ወጣቱ ትውልድ ከትናንት ጀግኖች አባቶቹ የሚማራቸው በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ በማንሳት።

በኢትጵያውያን አርበኞች የነፃነት ተጋድሎ የተበሰረው የአድዋ ድል በዓል 122ኛ አመት የዛሬ ሳምንት በመላው ኢትዮጵያውያን በድምቀት ይከበራል።

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 16 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ)