ዜና ዜና

ዓለም ዓቀፍ ሽብርተኝነት በየትኛው መንገድ ተቀባይነት የለውም- ዶ/ር ወርቅነህ

ዓለም አቀፍ አሸባሪነት በየትኛውም መንገድ ተቀባይነት የለውም ሲሉ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ተናገሩ።

አይ ኤስ አይ ኤስ ወይም ዳእሽ ተብሎ የሚጠራውን አሸባሪ ቡድን ሙሉ በሙሉ ለመደምሰስ የሚመክር ዓለም አቀፍ ጉባኤ በኩዌት እየተካሄደ ነው።

በጉባኤው ላይ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚነስትር ሬክ ቲለርሰንና የበርከታ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እየተሳተፉ ነው።

ዶክተር ወርቅነህ በዚሁ ወቅት፥ አይ ኤስ አይ ኤስ ወይም ዳእሽ ተብሎ የሚጠራውን አሸባሪ ቡድንን ሙሉ በሙሉ ለመደምሰስ የተቀናጀና በቁርጠኝነት የታገዘ ዓለም ዓቀፍ ትብብር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የዚህ የፀረ ሽብር ጥምረት አካል የሆነችው የዓለም ዓቀፍ እና የአካባቢያዊ ሽብር ኢላማ በመሆኗ ነው ብለዋል።

ዶክተር ወርቅነህ እንደገለፁት፥ ኢትዮጵያ ከምንጊዜውም በላይ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ቁርጠኛ መሆኗንና ለዓለም ሰላምና መረጋጋት ያላትን ታሪካዊ ሚና አጠናክራ ትቀጥላለች።

በዚህም ጉባዔ ላይ አሸባሪ ቡድኑን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት የሚያስችሉ ምክረ ሃሳቦች የሚቀርቡ ይሆናል።

እንዲሁም ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ተባብሮ መስራት የሚችልባቸው አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ተብሎ  ይጠብቃል።

የካቲት 6፣ 2010 /የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር