ዜና ዜና

ኢትዮጵያ አፍሪካን በተመለከቱ ውሳኔዎች ላይ አዎንታዊ ጫና እያሳደረች ነው - ዶክተር ተቀዳ

 ኢትዮጵያ የአፍሪካን ግጭቶች አስመልክቶ በመንግሥታቱ ድርጅት የሚተላለፉ ውሳኔዎች ላይ አዎንታዊ ጫና እያሳደረች መሆኑን በድርጅቱ የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይ ዶክተር ተቀዳ አለሙ ገለጹ።  

 ዶክተር ተቀዳ አገሪቷ በመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ባለፈው አንድ ዓመት ያከናወነቻቸውን ሥራዎች አስመልክቶ ከኢዜአ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። 

 ዶክተር ተቀዳ ኢትዮጵያ በምክር ቤቱ ውስጥ የአፍሪካን ጉዳይ በአንክሮ ስትከታተል መቆየቷን ነው የተናገሩት።

 በፀጥታው ምክር ቤት ከተመረጠችበት ጊዜ ጀምሮ ከአህጉሪቱ አባል አገራት ጋር በመሆን የጋራ አቋም በማንጸባረቅ እየሰራች መሆኑንም ነው የተናገሩት።

 በተለይም በአፍሪካ የጸጥታ ችግር በሚታይባቸው አገራት ምክር ቤቱ በሚያስተላልፈው ውሳኔ ላይ አዎንታዊ ጫና በማሳደር ጥረት እያደረገች መሆኑን ጠቁመዋል።

 ግጭት በተከሰተባቸው በተለይም በሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳንና በዳርፉር አካባቢዎች እስካሁን በምክር ቤቱ የተላለፉትን ውሳኔዎች ለአብነት አንስተዋል።

 በቀጣይም የሱዳንና የሶማሊያ ጉዳይ ምክር ቤቱ ትኩረት የሚያደርግባቸው የአህጉሪቱ የጸጥታ ጉዳዮች መሆናቸውንም ገልጸዋል።

 በምክር ቤቱ በተለይም ሠላምና ደህንነትን በተመለከተ በርካታ አስቸጋሪ ጉዳዮች ተገናዝበው ውሳኔዎች መተላለፋቸውን አስረድተዋል።

 ዶክተር ተቀዳ "በምክር ቤቱ ውሳኔ ማስተላለፍ ከባድ ሆኗል፤ ይህ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የፖለቲካ ሁኔታና የኃይል ሚዛን መለወጥን ተከትሎ የመጣ ነው" ብለዋል።

 ያም ሆኖ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በምክር ቤቱ ከነበራት አባልነት በላቀ ሁኔታ ኃላፊነቷን በአግባቡ እየተወጣች መሆኑን ነው የገለጹት።

 በተለይም በጸጥታ ሁኔታ ላይ ኢትዮጵያ በዓለም ወታደር ከሚያዋጡ አገራት መካከል ቀዳሚውን ደረጃ መያዟንና በዚህም በምሳሌነት እንደምትጠቀስ አስረድተዋል።

 በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፖለቲካ ውስጥ ልዩነት መፍጠር የምትችል አገር እንደሆነችም ጠቅሰዋል።

 ኢትዮጵያ በመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ስትሆን የአሁኑ ለሦስተኛ ጊዜ ነው።

 ከዚህ ቀደም እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር ከ1968 - 1969 እንዲሁም ከ1989 - 1990 ድረስ ለሁለት ጊዜ በአባልነት አገልግላለች።

የካቲት 6/2010/ኢዜአ