ዜና ዜና

ከ2 ሺህ በሚበልጡ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወሰደ

በመዲናዋ ከምግብና መጠጥ ጋር ባእድ ነገሮችን በመቀላቀልና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን ምርቶች ሲሸጡ በተገኙ 2 ሺህ 316 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ የምግብ፣ መጠጥ፣ የጤና አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታውቋል፡፡

 

ከበርበሬ ጋር ቀይ አፈር፣ ከእንጀራ ጋር የእንጨት ተረፈ ምርት (ሰጋቱራ)ና ጀሶ፣ ከፈሳሽ ዘይት ጋር ፋጉሎ ቀላቅሎ መሸጥ ዋና ዋናዎቹ ህገ ወጥ ድርጊቶች መሆናቸውም ተገልጿል፡፡

ባለስልጣኑ ለኢዜአ እንደገለፀው በበጀት ዓመቱ ታህሳስ እና ጥር ወራት ብቻ በመዲናዋ በሚገኙ 7 ሺህ 943 የምግብና የመጠጥ አገልግሎት ተቋማት ላይ የተቀናጀ ቁጥጥር አካሂዶ 1 ሺህ 772ቱ  ላይ እርምጃ ወስዷል፡፡

በባለስልጣኑ የቁጥጥር ንዑስ የስራ ሂደት ተወካይ አቶ አባዲ አብረሃ እንዳሉት እርምጃ ከተወሰደባቸው ተቋማት መካከል 212ቱ ሲታሸጉ 534ቱ የፅሁፍ፣ 1 ሺህ 26ቱ  ደግሞ የቃል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

የተቀናጀ ቁጥጥር ከተደረገባቸው 402 የምግብና መጠጥ አምራች ተቋማት ውስጥም 34ቱ የቃል፣ 37ቱ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ሲሆን 10ሩ መታሸጋቸውንም ነው አቶ አባዲ ያብራሩት፡፡

በ2 ሺህ 213 ጤና ነክ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ቁጥጥር ተደርጎ 463ቱ ላይ ከቃል ማስጠንቀቂያ እስከ ማሸግ የደረሰ እርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡

ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ እንሚያመለክተው በሁለት ወራት ውስጥ ከ14 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ የተበላሸ ምግብ እና ከ 11 ሺህ ሊትር በላይ የተበላሸ ምግብና መጠጥ ተወግዷል፡፡

ከ580 ሊትር በላይ ጤና ነክ ምርቶች እና ከ3 ሺህ 200 በላይ የተበላሹ ቁሳቁሶችም እንዲወገዱ ተደርጓል።

 የካቲት 5/2010/ኢዜአ