ዜና ዜና

የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት በመልካም ጅምር ላይ አንደሚገኝ ተገለጸ

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ)  ከፍተኛ አመራሮች የሚሳተፉበት ሁለተኛው ምዕራፍ የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት በመልካም ጅምር ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ።

ሁለተኛው ምዕራፍ የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት አስተዳደራዊ ጉዳዮችንና ቋሚ የሰላም ሁኔታ መፍጠርን አጀንዳው አድርጎ እ.ኤ.አ ከየካቲት 5 ቀን 2018 ጀምሮ እየተካሄደ ነው።

በደቡብ ሱዳን የኢጋድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ኢብራሂም ዋኢስ እንደተናገሩት  እስካሁን ባለው የውይይት ምዕራፉ መልካም የሚባሉ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

በድርድሩ ላይ የሚሳተፉ የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ሃይሎች የቀረበውን የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን አምባሳደር ኢብራሂም ዋኢስ ጠቅሰዋል።

"በአንድ አገር ውስጥ ሰላም ማስፈን ቀላል አይደለም" ያሉት ልዩ መልዕክተኛው፤ በውይይቱ መጨረሻም የተሻለ ውጤት እንደሚገኝ ያላቸውንም እምነት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዴኤታ ሒሩት ዘመነ በበኩላቸው 25 በደቡብ ሱዳን የሚንቀሳቀሱ የታጠቁና ያልታጠቁ የፖለቲካ ሃይሎች በውይይቱ እየተሳተፉ መሆኑን ተናግረዋል።

የሰነዱን የሃይል ክፍፍል በሚመለከቱ በርካታ አንቀጾች ላይ ወይይት እንደተደረገ የተናገሩት ሚንስትር ዴኤታዋ፤ ቋሚ የተኩስ አቁምና የፀጥታ ዘርፉ እንደገና በሚታይበት ሁኔታ ላይ በውይይቱ እየተሳተፉ ያሉ ሃይሎችና የመከላከያ አመራሮች በጋራ እንደሚመክሩበት ጠቁመዋል።

"በደቡብ ሱዳን ምርጫ ለማካሄድ ትክክለኛው ጊዜ መቼ ነው?" በሚለው ጉዳይ ላይም ውይይት ይደረጋል ነው ያሉት።

በውይይቱ ላይ እነዚህ ሃይሎች እርስ በርስ በመከባበር ቁጭ ብለው መደራደር መቻላቸው ትልቅ ስኬት መሆኑንም አመልክተዋል።

ከፍተኛ አመራሮች የሚሳተፉበት ሁለተኛው ምዕራፍ የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ላይ ከኢጋድ አባላት በተጨማሪ የአፍሪካ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታት እና ሌሎች አካላት እየተሳተፉ ሲሆን፤ ውይይቱ በሚቀጥለው አርብ እንደሚጠናቀቅም ታውቋል።

የመጀመሪያው ምዕራፍ ስምምነት እ.ኤ.አ ከታህሳስ 18 እሰከ 21 ቀን 2017 በአዲስ አበባ የተካሄደ መሆኑ ይታወሳል፡፡

የካቲት5/2010፤ኢዜአ