ዜና ዜና

የፀጥታ ኃይሉ ሠላም ከማስጠበቅ ባሻገር ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ ያጠናክራል

የፀጥታ ኃይሉ የአገሪቷን ሠላም ከማስጠበቅ ባሻገር ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የመከላከያ ሚኒስትር ሲራጅ ፈጌሳ ገለጹ።

6ኛውን የመከላከያ ሠራዊት ቀን አስመልክቶ የፀጥታ ኃይሎች ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ያላቸውን ድጋፍና ሕዝባዊነት ለመግለፅ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ዛሬ የእግር ጉዞ አድርገዋል።

በመዲናዋ ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከፌዴራልና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽኖች የተውጣጡ የፀጥታ ኃይሎች "የሕዳሴ ግድብ የሠላም ምንጭ ነው" በሚል መሪ ሃሳብ ከቴዎድሮስ አደባባይ እስከ መስቀል አደባባይ የእግር ጉዞ አካሂደዋል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ ሲራጅ ፈጌሳ የሕዳሴውን ግድብ የሠላም ዋንጫ ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ተረክበዋል።

ከርክክቡ በኋላ ባደረጉት ንግግር  የሕዝቡን ሠላምና ደኅንነትና የአገር ሉዓላዊነት ማስጠበቅ የሚችል፣ ሕገ መንግሥታዊ እምነቱ የፀና፣ ሙያዊና ሞራላዊ ሥነ-ምግባሩ የዳበረ የሠላም ኃይል መገንባት በመቻሉ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ጨምሮ ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ የታቀዱ የልማት ፕሮጀክቶችን በስኬት መፈፀም ተችሏል።

ከሕዝብ አብራክ የወጣ፣ የሕዝብ አገልጋይና ወገንተኝነት ያለው የፀጥታ ኃይሉ የልዕልና ማሳያ የሆነውን ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ሃሩርና ቁር ሳይበግረው እየጠበቀና የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ ሕዝባዊነቱንም እያሳየ ነው።

ግድቡ ከሚሰጠው የኤሌክትሪክ ኃይል በተጨማሪ በአገሪቱ የፈጠረው የ'ይቻላል' መንፈስ ኢትዮጵያዊያንን በአንድነት በማነሳሳት ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑንም ገልፀዋል።

ዋንጫውን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በማዘዋወር ሠራዊቱ ሕዝባዊነቱን ለማሳየትና ለግድቡ የሚያደርገውን ድጋፍ ለማስቀጠል የሚያግዝ  ንቅናቄ ከመፍጠር ባለፈ ሠራዊቱ ለግድቡ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀቱን የሚያሳይበት አጋጣሚ ነው ብለዋል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን አሁን ላይ ግንባታው 63 በመቶ መድረሱን ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

አዲስ አበባ ጥር 4/2010 /ኢዜአ/