ዜና ዜና

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ንቅናቄ በሠራዊቱ የእግር ጉዞ ተጀምሯል

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ የንቅናቄ ፕሮግራም የሠላም ጉዞ አዲስ አበባ ላይ በጸጥታ ኃይሎች የእግር ጉዞ ተጀምሯል።

"ሠላምና ህዳሴ ግድብ" በሚል መሪ ሐሳብ የሚከናወነው መርሃ ግብር የመጀመሪያ የሆነው የእግር ጉዞ ከቴዎድሮስ አደባባይ እስከ መስቀል አደባባይ ነው የተካሄደው።

ፕሮግራሙ የእግር ጉዞው ተሳታፊ የሆኑ የሠራዊት አባላት ባሰሟቸው የተለያዩ መፈክሮችና የተለያዩ ትርዒቶች ታጅቦ ተካሂዷል።

የንቅናቄ ፕሮግራሙ የተዘጋጀው ሠራዊቱ ለህዳሴው ግድብ ያለውን አጋርነት ለማሳየት መሆኑ ተገልጿል።

በእግር ጉዞው የተሳተፉት የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት፣ የፌደራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት ናቸው።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ከመከላከያ፣ ከፌደራልና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመሆን ያዘጋጁት

የንቅናቄ መርሃ ግብር ከዛሬ ጀምሮ በሚካሄዱ የተለያዩ ሁነቶች እንደሚቀጥል የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።

በተመሳሳይም የአማራ ክልል ፖሊስ ማርሽ ባንድ፣ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ከፍተኛ መኮንኖችና አባላት፣ የምዕራብ ዕዝ መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መኮንኖችና አባላት፣ የምዕራብ አየር ኃይል ምድብ ከፍተኛ መኮንኖችና አባላት እንዲሁም የአማራ ክልል ፖሊስ አድማ ብተና ከፍተኛ መኮንኖች በባህርዳር ከተማ የእግር ጉዞ አድርገዋል።

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 4 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ)