ዜና ዜና

የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት የሕዳሴውን ግድብ 7ኛ ዓመት በማስመልከት የእግር ጉዞ አደረጉ

የፀጥታ አካላት ሰላምን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ከዳር እንዲደርስ የሚያድርጉትን ሁሉን አቀፍ ተሳትፎና ድጋፍ ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ተጠቆመ።

የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበትን 7ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት ዛሬ የ4 ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞና የሰልፍ ትርኢት አድርገዋል።

የኦሮሚያ ክልል ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አማን አሊ በእዚህ ወቅት እንዳሉት የፀጥታ አካላት የክልሉን ሰላም የማስጠበቅ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።

ባለፉት ሰባት ዓመታት የክልሉ የፀጥታ አካላትን ጨምሮ የመንግስት ሠራተኞች፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ህብረተሰቡ ከ1 ቢሊዮን 850 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም የጸጥታ አካለት ሰላምን ከማስከበር ጎን ለጎን የግድቡ ግንባታ ከዳር እንዲደርስ እያደረጉ ያሉትን ሁሉን አቀፍ ተሳትፎና ድጋፍ አጠናክረው ማስቀጠል እንዳለባቸው አመልክተዋል።

የክልሉ ሕዝብና የፖሊስ አባላት በወቅታዊ የፀጥታ ችግር ሳይደናቀፉ ለግድቡ ግንባታ ከዳር መድረስ በጉልበት፣ በገንዘብና ባላቸው እውቀት የሚያደርጉት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በአሁኑ ወቅትም ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመዋል።

ከውስጥና ከውጪ በግድቡ ዙሪያ በአፍራሽ ኃይሎች  የሚናፈሱ አሉባልታዎችን ለማምከን ሕብረተሰቡ በአፈርና ውሃ እቀባ፣ በደን ልማትና በጥሬ ገንዘብ እያደረገ ያለውን ድጋፍ ከመቼው ጊዜ በላይ ማጠናከር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

በክልሉም ሆነ በሀገር ደረጃ አስተማማኝ ሰላም ለማረጋገጥና ልማቱን ለማስቀጠል የፀጥታ አካላት የተቀናጀ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያ ሥራ ሂደት ኃላፊ ኮማንደር ጉዲሳ ጉተማ ናቸው።

የክልሉ ፖሊስ አባላት የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ጊዜ አንስቶ ሁለት ጊዜ ቦንድ መግዛታቸውን ጠቅሰው፣ "ለግንባታው ከዳር መድረስ ከገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ ሰላምና ፀጥታን በማስከባር የላቀ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛሉ" ብለዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የፖሊስ አባላት መካከል ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ እንዳሉት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ ውጤት መሆኑን አመልክተዋል።

በመሆኑም የክልሉንም ሆነ የአካባቢውን ሰላም ወደ አስተማማኝ ደረጃ በማምጣት ለግንባታው ከዳር መድረስ በሙሉ አቅማቸው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ከዚህን ቀደም ለግድቡ ግንባታ ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ማድረጋቸውን ያስታወሱት ኮማንደር አስቻለው፣ በቀጣይም ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ በሙያም ሆነ በገንዘብ የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉበት ገልጸዋል።

የካቲት 4/2010  /ኢዜአ