ዜና ዜና

በኦሮሚያ ክልል የአካባቢ ብክለት ያስከተሉ አምስት ፋብሪካዎች ተዘጉ

የአካባቢ ብክለት ያስከተሉ አምስት ፋብሪካዎች መዝጋቱን የኦሮሚያ ክልል የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ገለጸ።

የባለስልጣኑ የአካባቢ አየር ንብረት ለውጥ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቦና ያዴሳ ለኢዜአ እንደተናገሩት በአካባቢ፣ በአየር፣ በውሃ እና በወንዞች ላይ ብክለት ሲያስከትሉ የነበሩ 5 ፋብሪካዎች እንዲስተካክሉ በተደጋጋሚ ቢጠየቁም ምላሽ ባለመስጠታቸው እንዲዘጉ ተደርጓል።

በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ ፋብሪካዎች ላይ ክትትልና ቁጥጥር አድርገናል ያሉት አቶ ቦና ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ለ619 ፋብሪካዎች ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆነ የአመራረት ስርአት እንዲከተሉ የጽሁፍ ግብረ-መልስ ተሰጥቷል ብለዋል።

በሰበታ ከተማ የሚገኘው አፍዴ የቆዳ ፋብሪካ ወደ ወንዝ ቆሻሻ በመልቀቅ እንዲሁም በቢሾፍቱ የሚገኙት የወንደር ፒቪሲ ማምረቻ እና ኤልፎራ የዶሮ እርባታ ድርጅት በሰራተኞች ጤና ላይ ጉዳት በማድረሳቸውና የአካባቢ ብክለት በማስከተላቸው መዘጋታቸውን ኃላፊው ተናግረዋል።

በክልሉ ሰሜን ሸዋ ዞን ኢደቡ አቦቴ ወረዳ የሚገኘው ኢስት ሲሚንቶ ፋብሪካ የሚያወጣው አቧራ እንዲሁም በጉጂ ዞን የሚገኘው የቀንጢቻ ታንታለም ማምረቻ ፋብሪካ በአካበቢና በሰው ላይ ጉዳት በማስከተላቸው በባለስልጣኑ የተዘጉ ተጨማሪ ፋብሪካዎች ናቸው።

ከተዘጉት 5 ፋብሪካዎች በተጨማሪ ለ126 ፋብሪካዎችና የልማት ድርጅቶች የመጀመሪያ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ለ40 ፋብሪካዎች የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ገልጸዋል።

"ይህን ስናደርግ ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ነው" የሚሉት አቶ ቦና ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ፣ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን ፣ ከኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲ ጋር በመሆን የክትትልና የድጋፍ ስራዎች መስራታቸውን ገልጸዋል።

ከእነዚህ ፋብሪከዎች የሚወጡ የተለያዩ ቆሻሻዎች አካባቢውን በመበከል፣በሰውም ሆነ በእንስሳት ጤና ላይ ጉዳት በማድረሳቸው ለረዥም ጊዜያት የመልካም አስተዳደደር ጥያቄዎችን ሲያስነሱ የቆዩ ናቸው።

ባለስልጣኑ ከኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ጋር በመሆን ከአካባቢ ጥበቃ ህግ አንጻር ፋብሪካዎች የሚሰሩትን ስራ ለማረጋገጥ በ20 ፋብሪካዎች ላይ የዳሰሳ ጥናት ማካሄዱን ገልጿል።

የጥናቱን ውጤትም የሚመለከታቸው አካላትና የፋብሪካዎቹ ባለቤቶች በተገኙበት ግብረ-መልስ የተሰጠ ሲሆን እያንዳንዱ ፋብሪካ የተሰጠውን ግብረ-መልስና ምከረ ሃሳብ በእቅድ እንዲያስተካክል እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

በሆለታ ከተማ የሚገኘው የአፍሪ አበባ ልማት ድርጅት እና ኢትዮ-ጃፓን የቆዳ ፋብሪካ በአካባቢ ላይ ባስከተሉት ችግር የተነሳ በባለስልጣኑ ከተዘጉ በኋላ ችግሩን የሚቀንሱና የሚያስቀሩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀማቸው ወደ ማምረት እንዲመለሱ ተደርገዋል።

ሌሎች በባለስልጣኑ የተዘጉ ፋብሪካዎች ከአካባቢው ጋር ተስማሚ የሆነ የአመራረት ስልት ከተከተሉና ዘመናዊ የቆሻሻና አያያዝ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ከጀመሩ ወደ ስራ መመለስ እንደሚችሉም ኃላፊው ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በአካባቢ ላይ ችግር እያስከተሉ በነበሩ 61 ፋብሪካዎች ላይ ከአካባቢ ህግ አንጻር በተደረገ የድጋፍና ክትትል ስራ እንዲሁም ከፋብሪካዎቹ ባለቤቶች ጋር በተካሄደ ውይይት 29ኙ ፋብሪካዎች መሻሻል አሳይተዋል ብለዋል።

የልማት ስራዎች ሲካሄዱ በአካባቢ፣ በማህበረሰብ እና በኢኮኖሚ ላይ የሚኖራቸውን ተጽዕኖ ከግምት ውስጥ ማስገባት ብቻ ሳይሆን በተግባር ማረጋገጥም የግድ መሆኑን አመላክተዋል።

የካቲት 3/2010 /ኢዜአ/