ዜና ዜና

በወጣቶች ተጠቃሚነት ላይ በጋራ ለመስራት በሚያስችል ጉዳዮች ላይ ዉይይት ተካሄደ

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ ርስቱ ይርዳ እና ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሐቢባ ሲራጅ፣ ከአለም አቀፍ የሰራ ድርጅትኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን እና የደቡብ ሱዳን አገራት ጸ/ቤት ዳይሬክተር እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት እና በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ልዩ ወኪል ከሆኑት ከሚስተር ጆርጅ ኦኩቶ እና የፕሮጀክት ዋና አማካሪ ከሚስ ሩቺካ ባህል እንዲሁም ከፕሮጀክት አስተባባሪ ከሆኑት ከአቶ አያሉ አድማስ ጋር በጽ/ቤታቸዉ በጋራ ለመስራት ዉይይት አካሂደዋል፡፡

ሚስተር ጆርጅ ኢትዮጵያ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የወጣቶች ፖሊሲና ስትራቴጂ በመንደፍና የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ በመመደብ እየሰራች መሆኑ አድናቆት እንዳላቸው ገልጸው ድርጅታቸው ይህን ተግባር ለማጠናከር እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ሚስ ሩቺካ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የወጣቶች ፖሊሲና ስትራቴጂ መኖሩና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎች ስራችንን ለመስራት የሚያቀልልን ቢሆንም የወጣቶች የስራ ዕድል መረጃና ድጋፍ በተጠናከረ መልኩ መስጠትን ይጠይቃል ፡፡ የአለም አቀፍ የሰራ ድርጅት በኢትዮጽያ ወጣቶችን የስራ እድል ፈጠራ ለማበረታታ በርካታ ስራዎችን በመስራ ላይ መሆኑን እና ድርጅቱ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ‘Addressing the Root causes of Migration in Ethiopia' የሚል ፕሮጀክት በመተግበር ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለዚህ ፕሮጀክት በስደት ተጋላጭ ክልሎች ማለትም በትግራይ፣ በአማራ፣በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክሎችና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማህበራዊና ኢኮኖሚዊ የዳሰሳ ጥናት ማካሄዳቸዉን ገልጸዋል፡፡ ፕሮጀክቱ የወጣቶች የስራ ዕድል መረጃ በመስጠትና በሌሎች ተዛማጅ ተግባራት ድጋፍ በማድረግ ወጣቶች የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በሚያስችል መልኩ እንሰራለን ብለዋል፡፡

ክቡር ሚኒስትር አቶ ርስቱ ይርዳ በበኩላቸው በፕሮጀክቱ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው ኢትዮጲያ ህገ ወጥ ስደትን ለመከላከል ብሔራዊ ኮሚቴ በማቋቋም ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ይህ ፕሮጀክት የተጀመረውን ስራ የሚያጠናክር በመሆኑ በጋራ ልንሰራባቸው እና ልንደጋገፍባቸው የምንችላቸውን ጉዳዮች በመለየት ወደ ስራ መግባት እንደሚገባ ጠቁመው ለዚህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

ጥር 30/2010/የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር /