ዜና ዜና

የድህረ ምርት ሰብሎችን አያያዝ የሚያሻሽል ስትራቴጂ ይፋ ተደረገ

የድህረ ምርት የምግብ ሰብሎችን አያያዝ የሚያሻሽል አዲስ ስትራቴጅ ይፋ ማድረጉን የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር አስታወቀ ፡፡

የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚንስቴር ትናንት ባካሄደው ውይይት ላይ ኢትዮጵያ በምግብ ሰብሎች የድህረ ምርት አያያዝ ችግር ምክንያት በየዓመቱ ከስምንት መቶ አርባ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገንዘብ ታጣለች፡፡

የጅማ ዩኒቨርስቲ የድህረ ምርት መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር አሊ ባረቀቡት ጥናታዊ ጽሑፍ እንደገለጹት በምርት ብክለትን ምክንያት ሀገሪቱ ከምታጣው የገንዘብ ኪሳራ በተጨማሪ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሚባክኑ ምርቶች ምክንያት አገልግሎት መስጠት እንዳይችል ሆኗል ተብሏል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባደረገው ጥናት መሠረትም በዋናነት ለብክነት የተጋለጡት የሰብል እህሎች ስንዴ፣ በቆሎ፣ ማሽላ እና ቦሎቄ ናቸው፡፡ የሰብል እህሎች አገራዊ የብክነት መጠን በዓመት ከ15-20 በመቶ ሲደርስ፤ በአጭር ጊዜ የሚበላሹ ደግሞ ከ35-40 በመቶ ይደርሳሉ፡፡

ለምግብ ሰብሎች ብክነት ዋነኛ ምክንያት ተብለው የተጠቀሱት የአርሶ አደሩ የሰብል አሰባሰብ ባህል፣ባህላዊ የእህል አወቃቅ ዘዴ እና ለረጅም ጊዜ የእህል ማከማቻ ቦታዎች ላይ ሰብሎችን ማስቀመጥ በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡

ይህንን ችግር ይቀርፋል የተባለ የድህረ ምርት የምግብ ሰብሎች አያያዝ ስትራቴጅ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ይፋ ተደርጓል፡፡

ስትራቴጂው በቀጣይ አምስት ዓመታት በመላ ሀገሪቱ ተግባራዊ የሚደረግ ሆኖ የማስፈጻሚያ የህግ ማዕቀፎች እንደሚወጡለት ተገልጿል፡፡

የካቲት 2/2010/ዋልታ/