ዜና ዜና

“የኢትዮጵያና ግብፅ ግንኙነት በናይል ውሃና በህዳሴ ግድብ ጉዳይ ብቻ የታጠረ አይደለም” ዶ/ር ወርቅነህ

ኢትዮጵያና ግብፅ በመካከላቸው ያለው ግንኙነት በናይል ውሃና በህዳሴ ግድብ ጉዳይ ብቻ የታጠረ አይደለም ሲሉ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ገለጹ።

ለ6ኛው የኢትዮ-ግብፅ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ ካይሮ የሚገኙት ዶ/ር ወርቅነህ ከግብፅ አቻቸው ሳሜህ ሽኩሪ ጋር በሁለትዮሽና በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ገንቢ ምክክር አድርገዋል።

የአገራቱ ግንኙነት ታሪካዊ ይዘት ያለው መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ ወደፊትም አገራቱ ያላቸውን እምቅ የትብብር ማዕቀፎች ማጠናከር እንዳለባቸው ተናግረዋል።

እንደ ዶክተር ወርቅነህ ገለጻ የአሁኑ ጉብኝታቸው ስላለፉ ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን ሁለቱን አገራትና ህዝቦች ወቅታዊና የወደፊት እድሎች ለማስፋት ነው።

ስድስተኛው የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ እስካሁን የተፈረሙ ስምምንቶችን ከመገምገም ባሻገር በቀጣይ የሚደረጉ የትብብር ማዕቀፎችንም ለመዳሰስ ቁልፍ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሽኩሪ በበኩላቸው ጉብኝቱ በአገራቱ መካከል በባህል፣ በትምህርት፣ በንግድና ኢንቨስትመት በማዕድንና በኢንዱስትሪ መስኮች ያለውን ትብብር ያሳድገዋል ብለዋል።

የአገራቱ ግንኙነት መጠናከር ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ብሎም ለአፍሪካ የትስስር ማዕቀፍ የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አስረድተዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ የአሁኑ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ለመጀመሪያ በመሪዎች ደረጃ መካሄዱ በሁለቱ አገራት መካከል የበለጠ ተቀራርቦና ተባብሮ ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያል።

የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባን ተከትሎ በፖለቲካ፣ በዲፕሎማቲክ፣ በቆንስላና በኢንዱስትሪ ጉዳዮች ዙሪያ የመግባቢያ ሰነድ እንደሚፈረም ይጠበቃል።

ጥር9/2010፤የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር