ዜና ዜና

የካፋ ቡና ባዮስፌር በዩኔስኮ ከተመዘገበ በኋላ የቡና ምርትና ምርታማነት መጨመሩን የዞኑ ቡና፣ ሻይ ቅመማ ቅመም ልማትና ግብይት ጽ/ቤት ገለፀ

የካፋ ቡና ባዩስፌር ሪዘርቭ በዩኔስኮ ከተመዘገበ በኋላ የቡና ምርትና ምርታማነት መጨመሩ አቶ ካሳሁን ታዬ በዞኑ ቡና ሻይ ቅመማ ቅመም ልማትና ግብይት ጽ/ቤት የቡና፣ ሻይ ቅመማ ቅመም የሥራ ሂደት አስተባባሪ ገልፀዋል፡፡

 

በዞኑ እስከ 2001 ዓ/ም ድረስ የጓሮ ቡና በ16ሺ 712 ሄክታር ማሳ ላይ የለማ ሲሆን ከ2002 ዓ/ም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የቡና ልማትን ለማስፋት በተደረገው የሕዝብ ንቅናቄ ከ149ሺ 419 ሄክታር በላይ የቡና ማሳ ማድረስ ተችሏል ብለዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ የቡና ምርት የሚሰጠው 38ሺ 288ሺ ሄክታር መሆኑም ተገልጿል፡፡

የካፋ ቡና ባዮስፌር ሪዘርቭ በዩኔስኮ ከመመዝገቡ ከ2002 ዓ/ም በፊት የጓሮ ቡና ምርታማነት በሄክታር ከ5 ኩንታል ያልበለጠ መሆኑን የገለጹት አስተባባሪው፣ በ2010 ዓ.ም የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የጓሮ ቡና ምረታማነት በአርሶ አደሮች ማሳ በአማካይ በሄክታር 9 ነጥብ 7 ኩንታል እንዲሁም በሞዴል አርሶ አደሮች ደግሞ ከ14 እስከ 21 ነጥብ 5 ኩንታል ምርት ማድረስ ተችሏል ብለዋል፡፡

በዞኑ በ2009 ዓ/ም የምርት ዘመን በክረምት ወራት 75 ሚሊዮን የቡና ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ 74 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኞች መተከላቸውንም አስተባባሪው ገልፀዋል፡፡

የካፋ ቡና ባዮስፌር ሪዘርቭ አላማው የዝርያ ብዝሃ ሕይወታዊ ጥበቃን፤ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትንና ተያያዥ ባህላዊ እሴቶችን በመንከባከብ ሞዴል አካባቢን ለመፍጠር ነው፡፡

የዘገባው የደቡብ ብ/ብ/ህ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው፡፡
ጥር 4/2010