ዜና ዜና

ኢትዮጵያ እና ኖርዌይ በስደተኞችና በስደተኞች ገዳይ አስተዳደር ላይ ተባብረው ለመስራት መስማማታቸው ተገለፀ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታዋ ሂሩት መለሰ እና የኖርዌይ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ሚኒስትር ሲልቪ ሊስቷንግን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እና ከጎረቤት ሃገራት በርካታ ስደተኞችን ተቀብላ ለማስተናገድ ያደራገችውን ጥረት እንዲሁም ህገ ወጥ ስደትን ለመከላከል እያከናወነች  ያለውን ስራ ሲልቪ ሊስቷንግ አድንቀዋል፡፡

ሚኒስትር ድኤታዋ ሂሩት መለሰ በበኩላቸው የስደተኞች ጉዳይ አለም አቀፍ አጀንዳ በመሆኑ ለስደት ምክንያት ለሆኑ መንስኤዎች ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

 በመሆኑም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤ የአፍሪካ ህብረትና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አለም አቀፍ ተቋማት ተባብረው መስራት እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ስደተኞችን በመቀበል ከአፍሪካ ቀዳሚ መሆኗንና የስደተኞችን ሰብዓዊ መብትና መሰረታዊ ፍላጎቶችን በማሟላት አስፈላጊውን እንክብካቤ በማድረግ ላይ ነች ብለዋል፡፡

ኖርዌይ በስደተኞች ጉዳይ አስተዳደር ላይ ከሌሎች የአውሮፓ ሃገራትና ከኢትዮጵያ ጋር ተባብራ ለመስራት ቁርጠኛ ነች በማለት ሲልቪ ሊስቷንግ ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል፡፡

ሁለቱም አካላት በህገ ወጥ የስደተኞች አዘዋዋሪዎችን ለህግ ለማቅረብና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ አብረው ለመስራት ተስማምተዋል ሲል ኢቢሲ የውጭ ጉዳይ ሚንስትርን ጠቅሶ ዘግቧ።

ጥር 04፡2010