ዜና ዜና

በምስራቅ ወለጋ ዞን በእንስሳት መኖ ልማት ላይ የተሳተፉ ወጣቶችና አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገለጹ፡፡

በጉቶ ጊዳ ወረዳ ሎኮ ቀበሌ በማህበር ተደራጅተው በእንስሳት መኖ ልማት የተሰማሩ ወጣቶች እንደገለጹት የመኖ ልማት ሥራ አዋጪ በመሆኑ የማህበሩ አባላትን ተጠቃሚ ያደረገ ነው።     

 የማህበሩ ሊቀመንበር ወጣት ደኑ ታሪኩ እንደገለጸው በእንስሳት መኖ ልማት ለመሳተፍ  ከመንግስት 7 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ጠይቀው ተሰጥቷቸዋል።

 በ2 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ ካለሙት የእንስሳት መኖ 12 ሺህ 500 ብር ገቢ ማግኘታቸውን ገልጸው በቀጣይ የተረከቡትን መሬት ሙሉ በሙሉ በእንስሳት መኖ ለመሸፈን መዘጋጀታቸውን ተናግሯል፡፡

 ከእንስሳት መኖ ሽያጭ በተጨማሪ ከሰበሰቡት 150 ኪሎ ግራም የሣር ዘር ሽያጭ ከ30 ሺህ ብር በላይ ገቢ ለማግኘት ማቃዳቸውንም ወጣት ደኑ ገልጿል፡፡

 በወረዳው የቅጤሳ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ አርሶ አደር ገለታ ገነቲ በበኩላቸው፣ በአንድ ሄክታር መሬት ላይ "ሮደስ፣ ደሾና የዝሆን ሳር" የተባሉ  የእንስሳት መኖ ዝርያዎችን እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

 የመኖ ልማቱ በበጋ ወራት የሚያጋጥመውን የእንስሳት መኖ ችግር እንዲቋቋሙ ያደረጋቸው መሆኑን ገልጸው፣ ከሣር ዘሮች ሽያጭ 15 ሺህ ብር ገቢ ለማግኘት አቅደው እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

 በአካባቢው የእንስሳት መኖ ልማት ሥራ በግንባር ቀደም አርሶ አደሮች ማሳ ላይ ከሦስት ዓመት በፊት እንደተጀመረ የገለጹት ደግሞ በዞኑ የልማት ጣቢያ ሠራተኛ አቶ ቶላ ዓለሙ ናቸው።

 በርካታ አርሶ አደሮች እርስ በርሳቸው ልምድ እየተለዋወጡ በግል ማሳቸው ሳይቀር ልማቱን በማስፋፋት ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን የገለጹት አቶ ቶላ፣ በእዚህም ከዘር ሽያጩ የውስጥ ገቢያቸውን በማሳደግ ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።

 በተለይ "ደሾ" የተባለው የእንስሳት መኖ የአፈርን ለምነትን ከመጠበቅ ባለፈ ለወተት ላሞች አስፈላጊ መሆኑን የተረዱ አርሶ አደሮች በስፋት ማልማት መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

 የዞኑ የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የእንስሳት መኖ ባለሙያ አቶ ደረጀ ከበደ በበኩላቸው ከ266 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በማሳቸው ላይ የተለያየ የእንስሳት መኖ በማልማት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

 እንደ ባለሙያው ገለጻ በዞኑ እየለማ ያለው የእንስሳት መኖ በ14 ሺህ 167 ሄክታር መሬት ላይ ሲሆን የመኖ ልማቱ አርሶ አደሩ ለእንስሳቱ መኖ እንዲያገኝ ከማድረግ ባለፈ ለወጣቶች የገቢ ምንጭ እየፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል።

ጥር3/2010/ኢዜአ