ዜና ዜና

ቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ከአንገት በላይ ህክምናዎችን በአዲስ መልክ ሊጀምር ነው

የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ከአንገት በላይ ህክምናዎችን ለመስጠት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎችን እያሟላ መሆኑን አስታወቀ።

በኮሌጁ የጤና አገልግሎት ምክትል ፕሮቮስት ዶክተር ብርሃኔ ረዳኢ ለኢዜአ እንደገለጹት ኮሌጁ አገር ወስጥ የሚሰጠውን ከአንገት በላይ ህክምና ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ህክምና ለመጀመር ዝግጅት እያደረገ ነው።

ኮሌጁ በ104 ሚሊዬን ብር ወጪ የአፍንጫ፣ የጆሮ፣ የጉሮሮ እና ተመሳሳይ ከአንገት በላይ ህክምናዎች  ዘመኑ በደረሰበት የቴክኖሎጂ ደረጃ መስጠት የሚያስችሉ ዘመናዊ መሳሪያዎችን ከውጭ አገራት ማስገባቱን ተናግረዋል።

የህክምና መሳሪያዎች ተከላ በመካሄድ ላይ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ብርሃኔ ህክምናውን በአዲስ መልክ በሶስት ወራት ውስጥ ለመጀመር እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት በኮሌጁ የሚሰጠው ከአንገት በላይ ህክምና መሳሪያዎች አለመሟላትና የቦታ እጥረት ችግሮች መኖራቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም ታካሚዎችን ቀልጣፋና በተሟላ ሁኔታ ማገልገል እንዳልተቻለ ገልጸው አገልግሎቱ በአዲስ መልክ መጀመሩ የህክምናውን ተደራሽነት ለማስፋፋት የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል።

በኮሌጁ ከአንገት በላይ ህክምና ድህረ ምረቃ መርሃ ግብር የሚከታተሉ ሰልጣኖችን ከዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ጋር ከማስተዋወቅና የስራ ላይ ልምምድን ከማስፋት አንጻር ያለውን ጠቀሜታም ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል በሆስፒታሉ እየተገነባ ያለው የካንሰር ህክምና ማዕከል ህንጻ ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ ቦታዎችን በማመቻቸት አገልግሎቱን ለመጀመር እየተንቀሳቀስን ነው ብለዋል።

የአስክሬን ምርመራ ህክምና፣ የህብለ ሰረሰር ቀዶ ህክምና፣ የቃጠሎ አደጋ ህክምና፣ የኩላሊት ህክምና፣ የፊኛና የሽንት ትቦ መስመር ህክምና እና ያለ ቀዶ ህክምና ጠጠሮችን የሚያስወግዱ ህክምናዎችን ካሳለፍነው መስከረም ወር አንስቶ በመሰጠት ላይ ይገኛል።

ጥር 3/2010፤ኢዜአ