ዜና ዜና

ሰላምና ፀጥታን ለማስፈን ኢጋድ የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ ይቀጥላል

ሕብረተሰቡን ከጎን በማድረግ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ፀጥታን ለማስፈን ኢጋድ የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢጋድ የሰላምና የፀጥታ ዘርፍ ዳይሬክተር ኮማንደር አበበ ሙሉነህ ተናገሩ፡፡

ሶማሊያን ከአልሻባብ ሽብርና ውድመት ነጻ ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ የሀገሪቱ የጎሳ መሪዎችና የሃይማኖት አባቶች ያላቸው ሚና ወሳኝ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) አልሻባብ የሚያራምደውን ፕሮፓጋንዳ ለመመከትና የሶማሊያን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ የሚያግዝ የሦስት ቀናት ስልጠና በድሬዳዋ እየተካሄደ ነው።

ከትናንት ጀምሮ እየተሰጠ ባለው ስልጠና ከሶማሊያ የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች፣ የጎሳ መሪዎችና ተቀባይነት ያላቸው ሴቶችና ግለሰቦች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢጋድ የሰላምና የፀጥታ ዘርፍ ዳይሬክተር ኮማንደር አበበ ሙሉነህ በዚህ ወቅት ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ለሦስት ቀናት የተዘጋጀው ስልጠና የአልሻባብን የተሳሳተ አካሄድና ፕሮፓጋንዳ የመመከት ዓላማ አለው።

በስልጠናው ሽብርተኞች ያነገቡትን የተሳሳተ አስተምህሮና ሃይማኖትን የተንተራሰ የእስልምና ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲረዱ ከማድረግ ባለፈ በቀጣይ ለሶማሊያ ሰላም የድርሻቸውን እንዲወጡ የማገዝ ግብ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡

ስለአልሻባብ ማንነት ተገቢው እውቀት እንዲያገኙ መደረጉ የአልሻባብን የሽብር ተግባርና የመስፋፋት እንቅስቃሴ ለመከላከል በሚደረገው ጥራት ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ሲባል ስልጠናው መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።

ኢጋድ ሕብረተሰቡን ከጎን በማድረግ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ፀጥታን ለማስፈን የሚያከናውናቸውን ተግባራት በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ኮማንደር አበበ  ገልጸዋል።

ሰልጣኞች የቀሰሙትን ትምህርት በቀጣይ ለማህበረሰቡ በማስተላለፍ የተሻለች ሶማሊያ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ህዝቡ የበኩሉን እንዲወጣ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ኬኒያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንና ኡጋንዳ በአሁኑ ወቅት የኢጋድ አባል ሀገራት ሲሆኑ ኤርትራ ራሷን ከአባል ሀገርነት በቅርቡ ማግለሏ የሚታወስ ነው፡፡

ጥር 3/2010፤ኢዜአ