ዜና ዜና

ጃፓን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የልማት ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጸች

ጃፓን ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር የምታከናውናቸው የልማት ስራዎች አጠናክራ እንደምትቀጥል የጃፓን አምባሳደር ሲንቺ ሳይዳ ገለጹ ፡፡

አምባሳደሩ ዛሬ በጃፓን አለም አቀፍ ትብብር (ጃይካ) ድጋፍ በጅማ ዞን የሚሰሩ የቡና እንዲሁም በመስኖ የሚለሙ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማቶችን  ጎብኝተዋል

በዞኑ በሰቃ ጨቆርሳ ወረዳ ኢትዮ ሸድ በመስኖ የሚያለማውን የአትክልትና ፍራፍሬ ልማትና በሸቤ ሰንቦ የሚካሔደውን የጫካ ቡና ልማትን  አምባሳደሩ ከጎበኟቸው መካከል ይገኙበታል፡፡

አምባሳደር ሺንቺ ሳይዳ በጉብኝታቸው ወቅት እንደገለጹት የጅማ ዞን ለምለምና ለየትኛውም አይነት የግብርና ስራ ምቹ በመሆኑ የአካባቢው አርሶአደሮች የተፈጥሮ ስጦታቸውን በአግባቡ በመጠቀም ኑሯቸው መለወጥ ይገባቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎቹን የመካከለኛ ገቢ ባለቤት ለማድረግ ያስቀመጠውን ግብ ለማሳካት በሚያደርገው እንቅስቃሴ የጃፓን መንግስት ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል ።

"ለወደፊቱም የጅማ ዞን አርሶአደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ በጋራ እንሰራለን "ብለዋል፡፡

የጅማ ዞን የሚመረተው የተፈጥሮ ቡና በጃፓን የሚወደድና ልዩ  ጣዕም ያለው በመሆኑ በሀገራቸው የገበያ አድማሱን ለማስፋት ጥረቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

ለአርሶአደሩ ሰፊ  የገበያ አማራጭ ከመሆን ባለፈ የቡና ጥራትን በማስጠበቅ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችል የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ድጋፍ እንደሚደረግም አምባሳደሩ አስታውቀዋል።

የኦሮሚያ ክልል መስኖ ልማት ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ  አቶ ሰይፈዲን ማሃዲ  በበኩላቸው የጃፓን መንግስት የኢትዮጵያን  የመስኖ ልማት እየደገፈ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ልማቱን ለማሳደግ በዕውቅትና በቴክኖሎጂ ሽግግር መስክ ጃፓን የምትሰጠው ድጋፍ  ህብረተሰቡን  ከድህነት ለመውጣት የሚያደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ጠቅሰዋል፡፡

በሸቤ ወረዳ 12 ቀበሌዎች መካከል የቡና ጣዕም ውድድር የተካሄደ ሲሆን አሸናፊዎቹም በጃፓንና በኢትዮጵያ ባለሙያዎች ተመርጠዋል፡፡

በውድድሩ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ የወጡት በከዱኬ ፣ ወንተሎና ሃሪሬ ቀበሌዎች በቀጥታ ምርታቸውን ወደ ጃፓን የሚልኩበት እድል እንደሚፈጠርላቸው በስነ ስርዓቱ ላይ  ተገልጻል፡፡

አንደኛ የወጣው የከዱኬ ቀበሌ ነዋሪው አቶ ጀበል አባሲመል በሰጡት አስተያየት "ለቡና ጥራት የሰጠነው ትኩረት አሸናፊ አድርጎናል" ብለዋል፡፡

በውድድሩ ላይ ተሳትፈው  ያልተሳካላቸው የሰንቦ ቀበሌ ነዋሪው አቶ አባዋሪ አባጀበል በበኩላቸው ቀበሌያቸው  ባያሸንፍም ውድድሩ ከቡና ገበያ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ወቅት እየደረሰ መምጣቱን እንደሚጠቁምና በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን  ተናግረዋል ፡፡

" በአሁኑ ወቅት የተለያዩ  ቡና ገዥዎች  ከአሜሪካ፣ ከጣሊያንና ከጃፓን  ወደ አካባቢችን  እየመጡ ስለሆነ ከእኛ የሚጠበቀው ጥራት ያለው ቡና ማምረት ብቻ ነው "ብለዋል፡፡

ጥር 3/2010፤ኢዜአ