ዜና ዜና

የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ተጀመረ

የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከፍተኛ አመራሮች ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ዛሬ በመቐለ ከተማ ተጀምሯል።

የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በኮንፈረንሱ መክፈቻ ስነ ሰርአት ላይ እንደተናገሩት፥ 35 ቀናት በወሰደው የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ግምገማ የድርጅት የውስጥ ችግር በጥልቀት ታይቷል።

በዚህ ግምገማ የአመራሩ ደክመት ድርጅቱን እንደጎዳው እና የበላይ አመራሩም በዚህ ሲገመገም ብዙ ጉድለት እንደተገኘበት ነው ያመለከቱት።

በዚህም የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ማእከላዊ ኮሚቴው ላካሄደው ግምገማ አጋዥ በመሆን በግምገማው ያልታዩ የሚባሉትን አዳዲስ ሃሳቦች እንዲያነሱ ይጠበቃል ብለዋል።

ኮንፈረንሱ ህወሓት ከድክመቱ እንዲወጣ ለማገዝ፣ ከሁሉም የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት እና ለመደጋገፍ ወሳኝ እንደሆነም ነው ዶክተር ደብረፅዮን ያነሱት።

ህወሓት በህዝብ ዘንድ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ቆርጦ መነሳቱን በመግለፅ፥ የወጣቶች የስራ አጥነት ችግሮችን ለመፍታት ከወጣቶች ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ምሁራንን በማሳተፍ ለልማት እና ዴሞክራሲ እድገት የሚያግዙ ጥናት እና ምርምሮች እንደሚካሄዱ በመክፈቻ ስነ ስርአቱ አስታውቀዋል።

ዛሬ በተጀመረው ኮንፈረንስ ቁጥራቸው 2 ሺህ 500 የሚደርሱ አመራሮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

ለተከታታይ ስምንት ቀናት የሚካሄደው ይህ ሰባተኛው ዙር ድርጅታዊ ኮንፈረንስ፥ ከኢህአዴግ እህት ድርጅቶች የሚታደሙ 200 አመራሮች በእንግዳነት እየተሳተፉ ሲሆን፥ ዶክተር ደብረፅዮን ሁሉም አመራር እና ተሳታፊ በነፃነት ሀሳቡን እንዲያቀርብ ነው ጥሪ ያቀረቡት።።

ሰባተኛ ደርጅታዊ ኮንፈረንሱ የጥልቅ ተሃድሶ ሂደቱ ተጠናክሮ የሚቀጥልበት ሲሆን፥ በክልሉ እና በሀገሪቱ አንዣቦ ያለውን አደጋ በሚገባ ገምግሞ መፍትሄ እና ቀጣይ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተገልጿል።

በዚህም የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ፥ ድርጅቱ ዳግም ጠንክሮ የሚወጣበት ታሪካዊ ኮንፈረንስ እንደሚሆን ይጠበቃል ነው የተባለው።

የህወሓት ስራ አስፃሚ ኮሚቴ በቅርቡ ያካሄደውን ስር ነቀል ግምገማ፣ ሂስና ግለ ሂስን ተከትሎ ዘጠኝ አባላት ያሉት የድርጅቱን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫን ማካሄዱ ይታወቃል።

ጥር 3፣ 2010(ኤፍ.ቢ.ሲ)