ዜና ዜና

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለኢትዮጵያ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች የፋይናንስ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታወቀች።

ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2020 በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በሚካሄደው ኤክስፖ ላይ እንደምትሳተፍም ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ መንሱር ቢን ዛይድ አል-ናህያን ጋር በሁለትዮሽና አካባቢያዊ ጉዳዮች ዙሪያ መወያያታቸውን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት አስታውቋል።

ኢትዮጵያ በመሰረተ ልማት ግንባታና በተለያዩ መስኮች የምታካሂደውን የልማት ጥረት እንደምትደግፍ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ መንሱር ገልጸዋል።

በዚህ መሰረትም ከጌዶ-ለምለም በረሃ እየተካሄደ ያለው የመንገድ ግንባታ እንዲጠናቀቅና ሌሎች የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች እንዲሰሩ አገራቸው የገንዘብ ድጋፍ እንደምታደርግ ተናግረዋል።

ዶክተር ወርቅነህ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እየተመዘገበ መሆኑን ጠቅሰው መንግስት ይህንን ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ሁለቱ ባለስልጣናት በሁለትዮሽና በአካባቢያዊ ጉዳዮች ጥልቅና ፍሬያማ ውይይት ማካሄዳቸውን መግለጫው አትቷል።

በተያያዘ ዜና ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2020 በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በሚካሄደው ኤክስፖ ላይ እንደምትሳተፍ ተጠቅሷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሪም አል ሀሽም ጋር መወያየታቸውን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መግለጫ ያመለክታል።

ዶክተር ወርቅነህ በውይይቱ ወቅት እንዳሉት እ.አ.አ በ2020 በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በሚካሄደው ኤክስፖ ኢትዮጵያ የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጁ ናት።

እንዲሁም አገሪቷ ኤክስፖው እንዲሳካ ከተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች ጋር ተባብራ እንደምትሰራ ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሪም አል ሀሽም በበኩላቸው ኤክስፖው አገራቸውን ከዓለም ማህበረሰብ ጋር ለማስተሳሰር የሚረዳ ነው ብለዋል።

ኤክስፖው ኢትዮጵያ ያላትን ባህል፣ታሪክ፣ወግ ለማሳየትና የኢንቨሰትመንት አቅሟን ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ሚኒስትሩ መግለጻቸው በመግለጫው ተመልክቷል።

በተያያዘም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ አቡዳቢ ከሚገኘው ኢግል ሂልስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሚስተር ዳግላስ ስሞል ጋር ውይይት አድርገዋል::

ኩባንያው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ እንደሚረዳና በአገሪቷ በቤት ግንባታ እና በተለያዩ የስራ መስኮች መዋዕለ ንዋዩን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳለውና ለዚህም ዝግጁ እንደሆነ ሃላፊዎች ገልጸዋል።

ዶክተር ወርቅነህ ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ እንዳላት በማስረዳት መንግስት አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግ መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መግለጫ አመላክቷል።

የሁለቱ አገራት ግንኙነት ከተጀመረ የቆየ ቢሆንም ኢትዮጵያ ቆንስላዋን እ.ኤ.አ በ2004 በዱባይ የከፈተች ሲሆን፤ ኤምባሲዋን ደግሞ በ2014 በአቡዳቢ ከፍታለች። የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ደግሞ እ.ኤ.አ በ2010 ነበር ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ የከፈተችው።

የኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የንግድ ግንኙነት ከ10 ዓመት በፊት ከነበረበት 45 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር እ.ኤ.አ በ2016 በዓመት ከ809 ሚሊዮን ዶላር በላይ መድረሱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ ያስረዳል።

ጥር 2/2010፤ኢዜአ