ዜና ዜና

የጦር መሳሪያዎች ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ሊገቡ ሲሉ በቁጥጥር ስር ውለዋል - ብሔራዊ የፀጥታና ደሕንነት ምክር ቤት

በኢትዮጵያ በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን አለመረጋጋት በመጠቀም የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ሲሞከር በቁጥጥር ስር መዋሉን ብሔራዊ የፀጥታና ደሕንነት ምክር ቤት አስታወቀ።

በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው ሁከት ተወግዶ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ከማድረግ አኳያ ሕብረተሰቡ የላቀ ተሳትፎ ማድረጉንም ምክር ቤቱ አስታውቋል።

የመከላከያ ሚኒስትሩና የምክር ቤቱ ኃላፊ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ዛሬ የምክር ቤቱን ሁለት ወራት አፈፃፀም አስመልክቶ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፤  በአገሪቷ በተወሰኑ አካባቢዎች የተከሰቱትን ሁከትና ብጥብጦችን ለማስቀጠል በተለዩ መንገዶች ጥረቶች ይደረጉ ነበር።

በተለይም ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችን የማስገባትና በተለያየ መንገድ ሁከትና ብጥብጡን ለማስቀጠል የሚደረጉ ጥረቶች እንደነበሩ የጠቆሙት አቶ ሲራጅ፤ ይሕንን ከማስቆም አኳያ "የፀጥታ አካላቱ  ከፍተኛ ተግባራትን አከናውኗል" ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በተለይ የመሳሪያ አያያዝና አጠቃቀምን አስመልክቶ አገራዊ የሆነ አዋጅ ለማውጣት ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑንም አቶ ሲራጅ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል አሁን ባለው ሁኔታ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች የተሻለ መረጋጋትና ሰላም እየሰፈነ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም የመላው ሕዝብ፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የአባገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች ተሳትፎ የጎላ እንደነበር አብራርተዋል።

እስካሁን በነበረው ሒደትም ሕብረተሰቡ ሰላም እንዲረጋገጥ፣ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን፣ ወንጀለኞች ለሕግ እንዲቀርቡና ወጣቶች በየአካባቢው አስተሳሰባቸውን አስተካከለው ትክክለኛውን መንገድ እንዲይዙ በማድረግ በኩል አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

ኢ.ዜ.አ አዲስ አበባ ጥር 2/2010