ዜና ዜና

ሰላም ለማስፈን ጠንካራ እርምጃ ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እንደሚጠብቁ የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ

ሰላም በዘላቂነት ለማስፈን የሚያስችል ጠንካራ ተግባራዊ እርምጃ  ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እንደሚጠብቁ በጅግጅጋ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

ነዋሪዎቹ እንዳመለከቱት የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ግምገማ  መጠናቀቁን ተከትሎ በአራቱ አባል ድርጅቶች ሊቀመናብርት በመገናኛ ብዙሃን የሰጡትን መግለጫ ተከታትለዋል፡፡

የጋራ መግለጫው በአሁኑ ወቅት የሚታየውን ያለመረጋጋት ለማስተካከል የሚረዳ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል፡፡

በከተማው የዜሮ አንድ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሐሊማ ዓብዲ በአካባቢያቸው ተፈጥሮ የነበረውን የጸጥታ ችግር  ዳግም እንዳይኖር ኢህአዴግ ባደረገው ሰብሰባ ቁርጥ ያለ መፍትሔ ይዞ ይመጣል ብለው ተስፋ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

በሰብሰባው የተላለፉት ውሳኔዎች በፍጥነት ተግባራዊ እንዲሆኑ ይፈልጋሉ፡፡

በኦሮሚያና በሶማሊ አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰቱ ግድያዎች የተጠረጠሩ ጥፋተኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ ውሳኔ መስጠቱ እንደሚደግፉ ወይዘሮ ሐሊማ ገልጸዋል፡፡

"ለዓመታት በፌዴራሊዝም ስርዓት ተሳስርን በመቻቻል ጠንካራ ኢኮኖሚ እየፈጠርን ብንቆይም በአሁኑ ወቅት ሀገራችንን ለአደጋ የሚያጋልጥ ሁኔታ ብቅ ብሏል" ያሉት ደግሞ በከተማው የቀበሌ ዜሮ አምስት ነዋሪ  አቶ አቡበከር መሀመድ ናቸው፡፡

ይህንን ችግር ለማስቆም እና ሰላም ለማስፈን የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በውሳኔያቸው መሰረት ሊተገብሩት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የህብረሰቡ የልማት፣የፍትህና የስራ አጥነት ችግሮች ለመፍታት ብሔራዊ ድርጅቶቹ በአንድ አቋም ተስማምተው መግባባት ላይ መድረሳቸው  እንደሚደግፉ የገለጹት   አቶ አቡበከር ወደ ተግባር በመግባት ሰላም ለማስፈን ጠንካራ እርምጃ ከድርጅቶች እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡

የብሔራዊ ድርጅቶቹ ግምገማ  ውጤት ከመቼውም ጊዜ የበለጠ የበሰለ ውሳኔ የተላለፈበት ነው የሚል እምነት እንዳላቸው የተናገሩት ደግሞ በከተማዋ የቀበሌ ዜሮ ስድስት  ነዋሪ አቶ መሐመድ አቢብ ናቸው፡፡

እንደሳቸው ገለጻ  ወጣቱ በሁሉም ዘርፍ ተሳታፊ ማድረግ ግዴታ በመሆኑ ድርጅቶቹ በዚህ ጉዳይ ተስማምተው ለውጥ ለማምጣት ቁርጠኛ መሆናቸው አስደስቷቸዋል፡፡

ታህሳስ 29/2010፤ኢዜአ