ዜና ዜና

የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ለህዳሴው ግድብ ግንባታ እያደረጉ ያሉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለፁ፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ም/ቤት ጽ/ቤት ከኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ፎረም ጋር በመተባበር በህዳሴው ግድብ ግንባታ ዙሪያ ለኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት የንቅናቄ መድረክ አዘጋጅቶ ውይይት አድርጓል፡፡

ዛሬ በኢትዮጵያ ሆቴል በተደረገው በዚህ ውይይት ላይ ንግግር ያደረጉት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ም/ቤት ጽ/ቤት ም/ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፍቅርተ ታምር የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት በሃገራችን ልማትና እድገት ላይ የራሳቸውን ጉልህ ድርሻ እያበረከቱ ነው ብለዋል፡፡

ወ/ሮ ፍቅርተ በንግግራቸው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ተሳትፎ አድርገዋል፤ ወደፊትም በገንዘብና በእውቀት፣ በህብረተሰቡ ዘንድ በሚደረጉ የንቅናቄ ተግባራት፣ ብሄራዊ መግባባትን በማጠናከርና በሌሎች መስኮች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡

በግድቡ ግንባታ ዙሪያ የሚስተዋሉ አሉታዊ አመለካከቶችን በመመከት ፣በውይይቶችና በጥናታዊ መድረኮች በመሳተፍ ብሎም የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ቦታው ድረስ ሄዶ በማየት የሲቪክ ማህበራት የልማት አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ ወ/ሮ ፍቅርተ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

በመድረኩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ እያደረጉት ያለው ተሳትፎ በ CCRDA ዋና ዳይሬክተርና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አስተባባሪ ዶ/ር መሸሻ ይትባረክ ቀርቧል፡፡

በኢትዮጵያ እስከ 2016 እ.ኤ.አ 3119 የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ተመዝግበው እየተንቀሳቀሱ ሲሆን ከአራት ሺ በላይ ፕሮጀክቶችን ቀርፀው ስራዎችን እየሰሩ ነው ብለዋል ዶ/ር መሸሻ፡፡

የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት እስካሁን ድረስ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከአካባቢ ጥበቃ ፣ ከግድብ ጉብኝት፣ የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎችና ሌሎች ተግባራት በተጨማሪ ከ 50 ሚሊዮን ብር በላይ የቦንድ ግዥ መፈፀማቸውን ዶ/ር መሸሻ  ገልፀዋል፡፡

የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ተሳትፎ ላይ ወደፊት የሚኖራቸው ሚናና አቅጣጫ ቀርቦ ውይይት የተደረገ ሲሆን የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ለህዳሴው ግድብ ግንባታ እያደረጉ ያሉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል፡፡

ታህሳስ 24/2010 /የኢፌዲሪ መ/ኮ/ጉ/ፅ/ቤት/