ዜና ዜና

ዶክተር ወርቅነህ ከብሪታንያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ጋር ተወያዩ

የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከብሪታንያው አቻቸው ቦሪስ ጆንሰን ጋር ተወያዩ።

ሁለቱ ሚኒስትሮች በኮት ዲቯር አቢጃን እየተካሄደ ከሚገኘው የአፍሪካ እና አውሮፓ ህብረቶች ስብሰባ ጎን ለጎን በሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

ዶክተር ወርቅነህ ብሪታኒያ በደቡብ ሱዳን ሰላም ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ድጋፍ እንድታደርግ እንፈልጋለን ብለዋል።

በውይይቱ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በደቡብ ሱዳን የሰላም ድርድር የሚፈለገው ውጤት እንዲመዘገብ እየሰራ መሆኑን ነው ዶክተር ወርቅነህ ለቦሪስ ጆንሰን ያነሱላቸው።

በዚህም በሰላም ሂደቱ ላይ አበረታች ውጤቶች እየታዩ መሆኑን ጠቅሰው፥ በመጪው ታህሳስ ወር በአዲስ አበባ የደቡብ ሱዳን የመጨረሻው ሁሉን አቀፍ የሰላም ድርድር እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።

የብሪታኒያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በበኩላቸው፥ ኢጋድ በደቡብ ሱዳን ለሚደረገው ሰላም የማስፈን ጥረት ሀገራቸው ሙሉ ድጋፏን እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።

ዶክተር ወርቅነህ በአቢጃን እየተካሄደው የሁለቱ አህጉራት ህብረቶች ስብሰባ ጎን ለጎን ከሱዳን፣ ከክሮሺያ እና ከኦስትሪያ አቻዎቻቸው ጋር በሁለትዮሽና በባለብዙ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ኤፍ ቢ ሲ የውጭ ጉዳይ ሚንስትርን  ጠቅሶ ዘግቧል ።

ህዳር21/2010