ዜና ዜና

ጠ/ሚ ኃይለማርያም በግብጽ የተፈፀመውን የሽብር ጥቃት አወገዙ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በግብጽ ሲናይ ግዛት በንጹሃን  ዜጎች  ላይ የደረሰውን የሽብር ጥቃት አወገዙ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ለግብጹ አቻቸው ሳሜህ ሽኩሪ የሀዘን መግለጫ ልከዋል።

በግብጽ ሲናይ ግዛት በመስጊድ የጸሎት ስነ ስርዓት በሚያካሂዱ ንጹሃን ዜጎች ላይ በተፈጸመው የሽብር ጥቃት በደረሰው የሞትና የመቁሰል አደጋ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ  የሀዘን መግለጫ ልከዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀዘን መግለጫቸው፣ የሽብር ጥቃቱ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ሊወገዝ የሚገባው እጅግ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት መሆኑን እና ሁኔታው መላው ዓለም የጸረ- ሽብር ትግሉን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው የሚያሳስብ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚሁ መልዕክታቸው፣ ለግብጽ ህዝብና መንግስት እንዲሁም ህይወታቸውን ላጡና ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ቤተሰቦች የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸው መጽናናትንም መመኘታቸውን ኢዜአ ዘግብል።

በግብፅ ሲናይ ታጣቂዎች በመስጊድ ላይ ባደረሱት ጥቃት የሞቱት ሰዎች ቁጥር 235 ደርሷል።

ጥቃቱ በቢር አል አቤድ ከተማ የዓርብ የአምልኮ ፕሮግራም ወቅት ነው የተፈፀመው። 

የአካባቢው ፖሊሶችም፥ በአራት ተሽከርካሪ የመጡ ታጣቂዎች ዋናውን መንገድ ለቀው ወደ መስጊዱ በመግባት ፀሎት በማድረስ ላይ በነበሩ አማኞች ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን ተናግረዋል።

በጥቃቱም ህይወታቸውን ካጡት በተጨማሪ ከ100 በላይ ሰዎች ላይም የተለያየ መጠን ያለው የመቁሰል አደጋ መድረሱን ነው ፖሊስ ያስታወቀው።

አዲስ አበባ፣ ህዳር 16፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ)