ዜና ዜና

ኢትዮጵያ ከሱዳንና ግብፅ ጋር በትብብር መስራቷን ትቀጥላለች- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ከሱዳንና ግብፅ ጋር ተባብራ መስራቷን እንደምትቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በግብፅ መገናኛ ብዙኃን እና በተወሰኑ የመንግስት ተቋማት በኩል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ እየወጡ ያሉ የተሳሳቱ መረጃዎች በግንባታው ሂደት ላይ ተፅእኖ እንደማይፈጥሩም ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ባለፉት 15 ቀናት በውጭ ጉዳይ ግንኙነት በተከናወኑ ስራዎችና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ጋዜጣዊ መግላጫ ሰጥቷል።

የህዳሴውን ግድብ አስመልክቶ በግብፅ በኩል እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሶስቱ አገራት መሪዎች የፈረሙትን መርሆዎች የሚጥስ መሆኑን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም ተናግረዋል፡፡

ትክክለኛውና ዘላቂው መፍትሄ ሁሉንም የአባይ ተፋሰስ አገራትን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስርአት መዘርጋት መሆኑንም ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል፡፡

አቶ መለስ አለም እንዳሉት፤ ሰሞኑን በተለያዩ የግብጽ መገናኛ ብዙሃን የአገሪቷን የስራ ኃላፊዎች ዋቢ እያደረጉ ስለ ህዳሴ ግድቡ ከእውነት የራቁና አፍራሽ መረጃዎችን በማሰራጨት ተደምጠዋል።

እነዚህን መረጃዎች ''የኢትዮጵያ መንግስት አፍራሽ አድርጎ ነው የሚመለካታቸው'' ያሉት ቃል አቀባዩ፤ አስተያየቶቹ የሱዳን፣ ግብጽና ኢትዮጵያ መሪዎች የተፈራረሙትን የመርህ ስምምነት የሚጥስ ነውም ብለዋል።

ሶስቱ አገሮች በታህሳስ 2007 ዓ.ም መተማመን፣ ጉልህ ጉዳት አለማድረስ፣ መረጃ መለዋወጥን ጨምሮ ሌሎች በሰባት ነጥቦች የመርህ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።

''በመሆኑም እነዚህ መርሆች እንዲከበሩም ኢትዮጵያ በአጽንዖት ትጠይቃለች'' ብለዋል።
እነዚያን መረጃዎች እንዳሉ በመቀበል የሚያራግቡ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እንዳሉ የጠቀሱት አቶ መለስ፤ ይህ ተገቢ ባለመሆኑ በኃላፊነትና አገራዊ ጥቅምን ባማከለ መልኩ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ግድቡን በራሷ አቅም እንደምትገነባ፣ ከግድቡ ሂደት ጋር በተያያዘ ደግሞ "ከሱዳንና ከግብጽ ጋር ተባብራ መስራቷን እንደምትቀጥል ሁሉም ማወቅ አለበት" ብለዋል አቶ መለስ።

''የግንባታው ጉዳይ ግን የማንም ፍቃድ የማይጠየቅበት፣ለኢትዮጵያ እድገት ወሳኝ በመሆኑ የህልውና እና የሞት ሽረት ጉዳይ ነው'' ብለዋል።
ቃል አቀባዩ በወቅታዊ ጉዳዮች መግለጫ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ባሳለፍነው ሳምንት በኳታር ያደረጉት የስራ ጉብኝትም "የሁለቱን አገሮች የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ሊያደርስ የሚችል ውጤታማ ጉብኝት ነው" ብለዋል።
የሁለቱ አገሮች መሪዎች የጋራ ጥቅሞችን ሊያስጠብቁ የሚችሉ የተለያዩ ስምምነቶች መፈረማቸው የአገራቱን ወዳጅነት እየጎለበተ መሄዱን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ከሴኔትና ኮንግረስ አባላት ጋር በሁለትዮሽ፣ክልላዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸውን አቶ መለስ ገልጸዋል።
ይህ መድረክ ኢትዮጵያ በቀጠናውና በአህጉሪቱ ሰላምና ትብብር እንዲሰፍን የምታደርገው ጥረት የተደነቀበትና በኢትዮጵያና አሜሪካ መካከል ያለውን ግንኙነት እንደሚያሻሽለውም ገልጸዋል።
ህዳር 14/2010 /ኢዜአ