ዜና ዜና

ለሕዳሴው ግድብ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የትግራይ ማዕከላዊ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ

ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በትግራይ ማዕከላዊ ዞን የሚገኙ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።

የዞኑ ታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሕዝብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት በበኩሉ በተያዘው ዓመት የመንግስት ሠራተኛና ባለሃብቶችን ሳይጨምር ከሕብረተሰቡ ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ለማሰባሰብ መታቀዱን አስታውቋል።

በዞኑ የታሕታይ ማይጨው ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አባል ሳጅን ሰለሞን ፍስሃ ለኢዜአ እንደተናገሩት ግድቡ የማንነት መገለጫ ከመሆኑ ባለፈ የአይቻልም አስተሳሰብን የሰበረ በመሆኑ ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ ሁለተናዊ ድጋፋቸውን ያጠናክራሉ።

በአሁኑ ወቅት ለሦስተኛ ጊዜ የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለመስጠት ቃል መግባታቸውን ገልጸው፣ የግንባታ ሥራው ሌት ተቀን ተከናውኖ አሁን የደረሰበት ደረጃ በመድረሱ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

በአክሱም ከተማ አስተዳድር በመንግስት መስሪያ ቤት አዲስ ተቀጠቀሪ እንደሆነ የገለጸው ወጣት ሸዊት ተወልደመድህን በበኩሉ የአንድ ወር ደመወዙን ለመጀመሪያ ጊዜ ለመስጠት ቃል መግባቱን ተናግሯል።

ለዚህ ታሪካዊ ፕሮጀክት መሳካት ሕብረተሰቡ እያደረገ ያለውን ርብርብ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የገለጸው ወጣት ሸዊት፣ ግደቡ ለዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ ባሻገር በቦንድ ግዥ የቁጠባ ባህልን ስለሚያሳድግ በቀጣይም ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጿል።
በዚህ ዓመት የ500 ብር ቦንድ ለመግዛት ዝግጅት ማድረጉን የተናገረው ደግሞ በአክሱም ከተማ በጫማ ጠረጋ ሥራ የሚተዳደረው ወጣት ሃይላይ ንጉስ ነው።

''ለግድቡ ግንባታ ቦንድ መግዛት መቆጠብ እንደሆነ ተረድቼያለሁ'' የሚለው ወጣት ሃይላይ ለግድቡ የአቅሙን አስተዋጽኦ በማድረጉ ኩራትና ደስታ እንደሚሰማው አመልክቷል።

ግድቡ ተገንብቶ እኪጠናቀቅ ድረስ በየዓመቱ አቅሙ የፈቀደውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናግሯል።
የዞኑ ሕዝብ ግንኙነት ምክትል ኃላፊ እና የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሕዝብ ተሳትፎ አስተባባሪ ወይዘሮ አበባ በለጠ በተያዘው ዓመት ከዞኑ ህዝብ ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ የሚውል 25 ሚሊዮን ብር የማሰባሰብ ዕቅድ መያዙን አመልክተዋል።

ለእዚህም በማይጨው የሕዳሴው ችቦ አቀባበል ስንስርዓትን ምክንያት በማድረግ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም እንደሚዘጋጅ ነው የጠቆሙት።
ገንዘቡ በሁሉም ቀበሌዎች አባወራና እማወራ ከ50 እስከ 100 ብር እንዲቆጥቡ በማድረግ የሚሰበስብ መሆኑንም የገለጹት ወይዘሮ አባባ በዕቅድ የተያዘው በዞኑ ያሉ የመንግስት ሠራተኞችና ባለሀብቱ የሚያዋጡትን እንደማይጨምር አስረድተዋል።
ህዳር 15/2010፤ኢዜአ