ዜና ዜና

የአፋር ክልል የመኖ ልማት የመንደር ማሰባሰብ ስራውን እያሳካ ነው

በአፋር ክልል የተጀመረው የመኖ ልማት አርብቶ አደሩን በመንደር ለማሰባሰብና ከእንስሳት የሚገኘውን ውጤት ለማሳደግ እያገዘ መሆኑን የክልሉ አርሶ አደርና ግብርና ልማት ቢሮ ገለፀ።

በክልሉ በዱብቲ ወረዳ ዳበልና ሀልቤሪ ቀበሌ 'ፓኒከምና ሮደስ' የሚሰኝ የተሻሻለ የእንስሳት መኖ ዝርያ በ700 ሄክታር መሬት በመልማት ላይ ይገኛል።

የመኖ ልማቱ በ2008 ዓ.ም ተከስቶ የነበረውን ድርቅ ለመቋቋም ታስቦ የተጀመረ ነው።

የቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሮ አባሂና ኮባ ለኢዜአ እንደተናገሩት በድርቁ ሳቢያ የተጀመረው የመኖ ልማት ከድርቁ በኋላም አርብቶ አደሩ ከቦታ ቦታ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ መግታት አስችሏል።

ከተመረተው የተሻሻለ የመኖ ዝርያ 40 ሺህ እስር ለአርብቶ አደሮች በነጻ መከፋፈሉን ገልጸዋል።

የመኖ ልማቱ አርብቶ አደሮቹ ከቦታ ቦታ በመዘዋወር ለከብቶቻቸው ምግብ በመፈለግ ሂደት የሚያባክኑትን ጉልበትና ጊዜ በመቆጠብ ማህበራዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እንዲያውሉትም አድርጓል።

በአብዛኞቹ የአገሪቱ ክልሎች በክረምት ወቅት ብቻ የሚለማው መኖ በአፋር ክልል በመስኖ መልማት መቻሉ የተለየ ያደርገዋል።

ለመኖ ልማቱ መጀመር የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር ከፍተኛ እገዛ ማድረጉንም የቢሮ ኃላፊዋ ገልጸዋል።

የቢሮው የኤክስቴንሽን ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዓሊ ዑመር በበኩላቸው መኖው ከክልሉ ፍጆታ ባሻገር ያልታሰረውንና በማሳ ላይ ያለውን ሳይጨምር 148 ሺህ ክምር በመኖ ባንክነት መከማቸቱን ተናግረዋል።

አርብቶ አደሮቹ የዘር ግብዓት ተሰጥቷቸውና የመኖ አጠቃቀም ስልጠና ወስደው ወደ ስራ መግባታቸውንና በመንግስት ከሚለማው በተጨማሪ በጓሯቸው እንዲያለሙ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ክልሉ ሰፊ የእንስሳት ሃብት ያለው በመሆኑ እየለማ ያለው መኖ በአርብቶ አደሩ ህይወት ላይ ለውጥ ለማምጣት ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

የአርብቶ አደሮቹን የመኖ ፍለጋ ዝውውር በማስቀረት ባሉበት ቦታ የተሻለ የእንስሳት አረባብ ዘዴን መተግበርም ያስችላቸዋል ነው ያሉት።

በክልሉ በአሁኑ ወቅት በቂ የእንስሳት መኖ የሚገኝ ሲሆን ባለፈው ዓመት በሱማሌ ክልል ድርቅ በማጋጠሙ የ15 ሺህ እስር የመኖ ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል።

ከዱብቲ በተጨማሪም በአሚባራ ወረዳ 40፣ በኡዋ ወረዳ ሱሉልታ ላይ 164፣ በዳሌፋጌ 30 እና ሃላይደጌ በምትባል ቦታ 15 ሄክታር መሬት ላይ የእንስሳት መኖ ልማት ማስፋፊያ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኢዜአ፣ ህዳር 5/2010