ዜና ዜና

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ዳያስፖራውን አነጋገሩ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በኳታር ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን አነጋግረዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ከትላንት ጀምሮ ኳታር ይገኛሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ የስራ ጉብኝታቸው ኢትዮጵያውያኑ ዳያስፖራ አነጋግረዋል።

በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ኢትዮጵያውያኑ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ላደረጉት አስተዋጽኦ አመስግነው፥ ይኸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

መንግስትም ለኮሚኒቲው አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ ለነበረው ግጭት ሰላም ለማስፈን እንደተቻለ እና የበለጠ ለማረጋጋት መንግስት ከህዝቡ ጎን ሆኖ ይሰራል ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ተናግረዋል።

ክቡር ሚኒስትሩ የአገሪቱ እድገት በአማካይ 10 ነጥብ 9 በመቶ ማደጉንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያኑ በበኩላቸው መንግስት በሳውዲ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ ላደረገው ጥረት አመስግነዋል።

የኮሚኒቲ ትምህርት ቤት በኳታር ለመክፈት እንዲቻል መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያውያኑ አገሪቱ ውስጥ ያለውን እድገትም ኣድንቀዋል።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት ከኳታሩ ኤሚር ሼክ ታሚም ቢን ሀማድ አልታኒ ጋር የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በሚጠናከሩባቸው ጉዳዮች ላይ እንዲሁም በአካባቢያዊ በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በሌላ ፕሮግራም ዛሬ ስለ ኳታር ፋውንዴሽን ማብራሪያ እንደሚሰጥም ከውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ህዳር 5፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ)