ዜና ዜና

ከፊል አርብቶ አደሮቹ በመስኖ ማልማት መጀመራቸው በአንድ ቦታ ተረጋግተው እንዲኖሩ አስችሏቸዋል

በመስኖ ማልማት መጀመራቸው በአንድ ቦታ ተረጋግተው እንዲኖሩ በማድረግ ህይወታቸውን መቀየር እንዳስቻላቸው በአፋር ክልል አዋሽ ወረዳ የሳቡሬ ቀበሌ ከፊል አርብቶ አደሮች ተናገሩ።

በክልሉ አርብቶ አደሮችን ከፊል አርብቶ አደር ለማድረግ በመንደር ማሰባሰብና በግብርና ላይ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

ቀድሞ ለከብቶቻቸው ውሃና ግጦሽ ፍለጋ ከቦታ ቦታ ይዘዋወሩ የነበሩት የቀበሌው ከፊል አርብቶ አደሮች በአሁኑ ወቅት በ250 ሄክታር መሬት ላይ በቆሎ፣ ሽንኩርት፣ ሃባብና ቲማቲም በመስኖ እያለሙ ነው።

የግብርና ስራ መጀመራቸው የራሳቸውንና የከብቶቻቸውን የምግብና የመኖ ፍጆታ ከማሟላት ባለፈ በተለያዩ ወቅቶች ግጦሽ ፍለጋ ከቦታ ቦታ በሚደርጉት ጉዞ ይደርስባቸው የነበረውን እንግልት እንዳስቀረላቸው ያነጋገራቸው ከፊል አርብቶ አደሮች ገልጸዋል።

መስኖ በመጠቀም ያመረቱት ምርት በሚያስገኝላቸው ገቢ የቤተሰቦቻቸውን ህይወት መቀየር እንደቻሉም ነው የተናገሩት።

የሳቡሬ ቀበሌ ዲዲጋ መንደር ነዋሪዋ አርሶ አደር ወይዘሮ አርባሂ አባአባ በአሁኑ ወቅት ቲማቲም፣ በቆሎና ሽንኩርት በማምረት ላይ እንደሚገኙ ይናገራሉ።

ከምርቶቹ በሚያገኙት ገቢም የቤተሰባቸውን ህይወት ከመቀየር አልፈው የባንክ ቁጠባ ሒሳብ መክፈት እንደቻሉ ገልጸዋል።

''መጀመሪያ ወደ ግብርና ስራ ስመጣ አስር መኪና ቲማቲም አምርቼ በኪሎ በ10 ብር ተነሳልኝ፣ ቀጥዬ ደግሞ በቆሎ ዘራሁ 80 ኩንታል አገኘሁ፣ በሶስተኛው ሽንኩርት ዘርቼ 160 ሺህ ብር ትርፍ አገኘሁ'' ነው ያሉት።

"ቀድሞ ለከብቶቻችን ምግብና ውሃ ፍለጋ ከቦታ ቦታ እንከራተት ነበር አሁን ይሄ የለም" ሲሉም አክለዋል።

ከቦታ ቦታ በመዘዋወር ይኖሩት የነበረው ህይወት ቀርቶ በሚኖሩበት ቀበሌና በአዋሽ ከተማ መኖሪያ ቤቶች መስራታቸውን ተናግረዋል።

ወይዘሮ አርባሂ "ተረጋግቼ መኖር በመቻሌ ሶስት ልጆቼን ወደ ትምህርት በመላክ 7ኛ፣ 8ኛ እና 9ኛ ክፍል ማድረስ ችያለሁ" ብለዋል።

ሌላው የዚያው መንደር ነዋሪ አርሶና አርብቶ አደር ፈንታሌ ኢናባ ወደ እርሻ ስራው በማዘንበላቸው ከቤተሰብ የምግብ ፍጆታ አልፈው ለገበያ የሚሆኑ ምርቶችን እያቀረቡ መሆናቸውን ይናገራሉ።

በቀበሌው የጋሪረባ መንደር ነዋሪው አርሶ አደር ሙሳ ፋተና በበኩላቸው እርሳቸውና ሌሎች የመንደሩ ገበሬዎች ከሽንኩርት ልማት ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ ገልጸዋል።

ኑሯቸውን በአንድ ቦታ በማድረጋቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ ህይወታቸው እየተለወጠ መሆኑንና በኩታ ገጠም በጋራ ማረስ በጀመሩ በጥቂት ጊዜ ውስጥም የተሻለ ምርት ማግኘት መቻላቸውን አስረድተዋል።

የአዋሽ ወረዳ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሳ ሀሰን በክልሉ አርብቶ አደሩን ወደ ከፊል አርብቶ አደርነት ለመለወጥ በመንግስት እየተደረገ ያለው ጥረት ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።

አርብቶ አደሩ በግብርና ስራ እንዲሰማራ መደረጉ በአንድ ቦታ ሆኖ በመስራት ህይወቱን እንዲለውጥ እያስቻለው ነው ብለዋል።

ለውጤታማነቱም ምርጥ ዘር፣ ትራክተር፣ የእጅ መሳሪያዎችና የውሃ መሳቢያ ሞተሮች ድጋፍ በነጻ እየተደረገ ነው።

የአርብቶ አደሩ ወደ ግብርና መግባት ለመንደር ማሰባሰብ ስራው ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል ያሉት አቶ ሙሳ ገበያ በማፈላለግ ምርቱን ከማሳው ላይ የሚገዙ ነጋዴዎችን የማምጣት ስራ በመንግስት በኩል ተሰርቷል ብለዋል።

ከአርሶ አደሮቹ የተነሳው የመሬት ጥበት ችግር መኖሩን በመቀበል ለጥያቄያቸው ምላሽ ለመስጠት ቦታ የመለየት ስራ እየተሰራ እንደሆነም አስታውቀዋል።

ህዳር 5/2010/ኢዜአ/