ዜና ዜና

ለአርሶ አደሩ የተሻሸሉ የግብርና የቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ ምርታማነቱን ለማሳደግ እየተሰራ ነው፡፡

ለአርሶ አደሩ የተሻሸሉ የግብርና የቴክኖሎጂዎችን በማቅረብና የአጠቃቀም ክህሎትን በማዳበር ምርታማነቱን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር  ዶክተር እያሱ አብርሃ ገለጹ።

 በምስራቅ ጎጃም ዞን አነደድና ደብረ ኤሊያስ ወረዳዎች በኩታገጠም የለማ  የስንዴና የጤፍ ሰብል ተጎብኝቷል።

 ሚኒስትሩ በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ያለው በሁለተኛው የእድገትና የትራንስፎርሜሽን ዘመን በተያዘው ዕቅድ መሰረት ነው።

 እስካሁን በተደረገው ጥረትም የኩታገጠም አሰራር እየዳበረ መምጣቱን ጠቅሰው  የማረሻ፣ የመዝሪያ፣ የመውቂያና የመስብሰቢያ ቴክኖሎጂዎችን በተደራጀ አግባብ ጥቅም ላይ ለማዋል ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን ገልፀዋል።

 እነዚህ ቴክኖሎጂዎች በማህበራትና በግል ባለሀብቶች እንዲቀርቡ በማድረግ ችግሩን እንዲያቃለል እየተደረገ ነው።

 በቀጣይም በኩታገጠም  ለሚለማ  የስንዴና የጤፍ ሰብል መሰብሰብ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ከውጭ በመግዛት ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ሚኒስትሩ አመልክተዋል።

 በምስራቅ ጎጃም የስንዴና የጤፍ ሰብል አርሶ አደሩ በኩታገጠም አሰራር በማልማት የተመዘገበው ለውጥ ለሌሎች አካባቢዎችም መልካም ተሞክሮ እንዲሚሆን ጠቁመዋል።

 የግብርና ስራው ከልማዳዊ አሰራር  በመላቀቅ ዘመናዊ ለማድረግ አርሶ አደሩ የሚፈልጋቸውን የተመረጡ ቴክኖሎጂዎች በማቅረብ እጥረቱን ለማፍታት መንግስት በትኩረትና በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

 የዞኑ ግብርና ልማት መምሪያ ኃላፊ  አቶ ፈንታሁን አቢታ በበኩላቸው የኩታ ገጠም አሰራር ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ በማሸጋገር የምርት እድገት ጭማሬ እንዲመጣ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡

 በዚህም የአርሶ አደሩን ግንዛቤ በማሳደግ ስንዴ፣ ማሽላ፣ ጤፍ፣ በቆሎ፣ ቦለቄና ቢራ ገብስ ላይ የኩታ ገጠም አሰራርን ተግባራዊ ተደርጓል፡፡

 "በ2009/2010 የምርት ዘመን በሰብል ከተሸፈነው ከ649 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ ከ226 ሺህ ሄክታሩ በኩታገጠም አሰራር በስንዴና ጤፍ ክላስተር የለማ ነው "ብለዋል።

 በዚህ አሰራር ከተሳታፊ አርሶ አደሮች መካከል የደብረኤሊያስ ወረዳ የጥጃ ጎጠር ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሙሉቀን ጸጋ እንዳሉት ግማሽ ሄክታር ማሳቸውን በኩታገጠም  ማልማታቸውና ከዚህም  ከ40 ኩንታል በላይ ምርት እየጠበቁ ነው።

 ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ በኩታ ገጠም ግማሽ ሄክታር ጤፍ ማልማታቸውንና ከዚህም 12 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን የተናገሩት ደግሞ የአነደድ ወረዳ አርሶ አደር ስፈራው ከበደ ናቸው።

 ይህም በተለምዶ አሰራር ከሚያገኙት በአራት ኩንታል ጭማሪ እንዳለው ጠቁመዋል።

 በዞኑ በመኸሩ ወቅት ከለማው መሬት ከ20ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል።

 ደብረ ማርቆስ ህዳር 4/2010(ኢዜአ)