ዜና ዜና

ለማሕበራትና ዩኒየኖች የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንደሚሰራ የትግራይ ክልል ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አስታወቀ

በትግራይ ክልል ለተቋቋሙ የምርጥ ዘር ብዜት ሕብረት ሥራ ማህበራትና ዩኒየኖች የተሻለ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ድጋፍ እንደሚያደርግ የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በማይጨው ከተማ የተቋቋመው የ"ሐድነት ራያ" የምርጥ የዘር ብዜት ሕብረት ሥራ ዩኒየን በ6 ሚሊዮን ብር ያስገነባቸውን አገልግሎት መስጫ ሕንጻዎች ትላንት አስመርቋል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ፍስሃ በዛብህ በወቅቱ እንደገለጹት በክልሉ ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በምርጥ ዘር ብዜት የተሰማሩ 60 የገበሬዎች የሕብረት ሥራ ማህበራት ተቋቁመዋል።

ማህበራቱ በተቋቋሙ አጭር ጊዜ ውስጥ የጀመሩት የምርጥ ዘር ብዜት ሥራ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።

ለእዚህም በ2008/2009 የምርት ዘመን 10 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ የተለያየ የሰብል ምርጥ ዘር ማምረታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

ይሁንና ላመረቱት ምርት የገበያ ችግር እንደገጠማቸው የገለፁት ኃላፊው፣ ለምርታቸው የገበያ ትስስር ለመፍጠር አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አስታውቀዋል።

አቶ ፍስሀ እንዳሉት፣ የወረዳ አስተዳደር ጽህፈት ቤቶች በየአካባቢያቸው የሚገኙ አርሶ አደሮችን የዘር ፍላጎት በመለየት ማህበራቱ ካቋቋሟቸው ዩኒየኖች ዘር በመግዛት የሚያቀርቡበት አቅጣጫ ተቀምጧል።

ለምርጥ ዘር ምርት ግዥ የሚውል ገንዘብም ከክልሉ መንግስት የሚመደብ ነው።

በተጨማሪም ማህበራቱ ለሚያከናውኗቸው ሥራዎች ማስፈጸሚያ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አመላክተዋል ።

ከእዚህ በተጨማሪ ማህበራቱ በመኸር ወቅት ብቻ የሚያካሂዱት የዘር ብዜት ሥራ በቂ ባለመሆኑ በበጋ ወቅት በመስኖ የታገዘ ልማት እንዲያካሂዱ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ጠቁመዋል።

በአምባላጌ ወረዳ ብርሃን አይባ የገበሬዎች የዘር ብዜት ሕብረት ሥራ ማህበር አባል ቄስ ግርማይ ሐጎስ በሰጡት አስተያየት በ2009/2010 የመኸር ወቅት በግማሽ ሄክታር ማሳቸው ላይ ምርጥ የስንዴ ዘር ማባዛታቸውን ተናግረዋል።

"ምርጥ ዘሩንም በማህበራቸው አማካኝነት በመሸጥ የተሻለ ገቢ ለማግኘት ተስፋ አድርጊያለሁ" ብለዋል።

የ"ሐድነት ራያ" የምርጥ የዘር ብዜት ሕብረት ሥራ ዩኒየን ካስመረቃቸው ሕንጻዎች ውስጥ 10 ሺህ ኩንታል የሚይዝ የምርት ማከማቻ መጋዘን እንዲሁም የዘር ጥራትና ብቅለት ሂደት ምርምራ ቤተ-ሙከራ ይገኝበታል፡፡

ኢዜአ፣ ማይጨው ህዳር 4/2010