ዜና ዜና

ሀሰተኛ የብር ኖቶችንና ሌሎች ማስረጃዎችን ያዘጋጃሉ የተባሉ ሁለት ግለሰቦች ተያዙ፡፡

ሀሰተኛ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር የብር ኖቶችንና ሌሎች የትምህርት ማስረጃዎችን ያዘጋጃሉ የተባሉ ሁለት ግለሰቦችን በመያዝ ጉዳያቸው በህግ እንዲታይ እያደረገ መሆኑን የአማራ ክልል ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ የምርመራና አቃቤ ህግ ዳይሬክተር አቶ ተመስገን መላክ እንደገለጹት ኮሚሽኑ ከህዝብ በደረሰው ጥቆማ መሠረት ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እንዲታይ እየተደረገ ነው።

ተጠርጣሪዎቹ የኢትዮጵያና የሌሎች ሀገራት የብር ኖቶችን እያተሙ በማሰራጨት የማጭበርበር ስራ ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ገልፀዋል።

ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ፣ የብቃት ምዘና፣ የስራ ልምድ፣ መንጃ ፈቃድና ሌሎች ሀሰተኛ ሰነዶችን በማተም የወንጀል ስራ ሲያከናውኑ እንደነበረም ተናግረዋል።

ከህብረተሰቡ የደረሰውን ጥቆማ መሰረት በማድረግ በተካሄደ የክትትል ስራ ግለሰቦቹ ከመስሪያ መሳሪዎቹና ካዘጋጇቸው ሰነዶች ጋር እጅ ከፈንጅ መያዛቸውን አመልክተዋል።

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ሲውሉም ተዘጋጅተው ያልተሰራጩ 620 ሃሰተኛ ባለመቶና አራት ባለ ሃምሳ የብር ኖት ፣ 162 ሀሰተኛ ባለመቶ የአሜሪካን ዶላርና መሰል የብር ኖቶች መያዛቸውን አስረድተዋል።

እንዲሁም የሳውዲ ሪያልና የህንድ ሩፒ ኖቶች መያዛቸውንም ጠቁመዋል።

በኢፌዴሪ የትምህርት ሚኒስቴር ሀገር አቀፍ ፈተናዎች ድርጅት ያልተሰጡ የ10ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናና የመሰናዶ ትምህርት ማጠናቀቂያ ውጤቶችን በመቀያየር የተሰሩ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችም ተይዘዋል።

በተለያዩ የግልና የመንግስት ኮሌጆች ስም የተዘጋጁ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች፣ መንጃ ፈቃዶችና የጤና ሙያ ፈቃዶች መያዛቸውንም ጠቁመዋል።

የ8ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ካርዶችና ሌሎች በርከት ያሉ የቀበሌ መታወቂያዎችን ለመስራት የሚያገለግሉ ሀሰተኛ ማስረጃዎችም ተገኝተዋል።

ለወንጀል መስሪያነት ሲገለገልባቸው የነበሩ ላብቶፕ፣ ዴስክቶፕ፣ ሁለት ባለከለር ፕሪንተሮች፣ አንድ ከለር አልባ ፕሪንተር፣ ፍሌሾችና የተለያዩ የማህተም አርማዎችና ሌሎች ቁሳቁሶች መያዛቸውንም አስታውቀዋል።    

በተለይም ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ፣ መንጃ ፈቃድና መታወቂያ ለመስራት ተጠርጣሪዎቹ የተቀበሏቸው የ48 ሰዎች ጉርድ ፎቶግራፎችም ተገኝተዋል።

ከሁለቱ ተጠርጣሪዎች በተጨማሪ ለጊዜው የተሰወረውን ተባባሪ ግለሰብ በቁጥጥር ስር አውሎ በፍርድ ተጠያቂ ለማድረግ የተጠናከረ የክትትል ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ህብረተሰቡም የሀገርን ጥቅም የሚጎዱ ድርጊቶችን የሚፈፅሙ ግለሰቦችን ሲመለከት ለሚመለከተው የፀጥታ አካላት የጀመረውን ጥቆማ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

ኮሚሽኑም በተጠርጣሪዎች ላይ ሲያደርግ የቆየውን ምርመራ አጠናቆ የሰነድ ማስረጃዎችን ወደአቃቤ ህግ መርቶ ክሱን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማቅረቡን አስታውቀዋል።

  ባህርዳር ህዳር 4/2010(ኢዜአ)