ዜና ዜና

አዲስ የካሳ ቀመር ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ፡፡

በሀገሪቱ ከካሳ አከፋፈል ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችን እንደሚፈታ የታመነበት አዲስ የካሳ ቀመር ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ።

ለተለያዩ የልማት ስራዎች ሲባል ከመሬታቸው እና ንብረታቸው የሚፈናቀሉ ዜጎች የሚከፈለው ካሳ በቂ አይደለም በማለት ተደጋጋሚ ቅሬታ ያሰማሉ።

ካሳው ከማነሱ ባሻገር በዘላቂነት የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ያመቻቸ አለመሆኑንም ይናገራሉ፤ ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘም ከተነሺዎች ጋር በሚፈጠሩ ችግሮች ፕሮጀክቶች ሲጓተቱ ይታያል።

የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋም፣ የቤቶች ልማት እና የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴርም በጋራ፥ በ19 97 ዓ.ም በወጣው የካሳ አከፋፈል አዋጅ እና ከሁለት አመት በኋላ በፀደቀው የአዋጁ ማስፈፀሚያ ደንብ ዙሪያ ጥናት አድርገዋል።

በጥናቱም አዋጁ የተወሰኑ ክፍተቶች እንዳሉበት መረጋገጡን፥ የፌደራል የተቀናጀ መሰረተ ልማቶች ማስተባበሪያ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ሰለሞን ገብረመድህን ተናግረዋል።

አርሶ አደሮች ለልማት ሲነሱ ምትክ ቦታ እና ገንዘብ ይሰጣቸዋል፤ ይሁን እንጅ ገንዘቡን ለዘላቂ ኑሯቸው እንዲጠቀሙበት ፓኬጅ ባለመዘጋጀቱ በርካቶች ገንዘቡን ጨርሰው እርዳታ ፈላጊ ሲሆኑ ይስተዋላል።

ሌላው አርሶ አደሩ ከመሬቱ ሲነሳ ከሰብል ምርት ሊያገኝ የሚችለው የአምስት አመቱ ምርት አማካይ ተሰልቶ በ10 አመት ተባዝቶ ይሰጠዋል፤ ይሁን እንጅ ከአማካዩ ይልቅ ከፍተኛው ሊወሰድ ይገባል የሚል ቅሬታ ሲያስነሳ መቆየቱን አቶ ሰለሞን ይናገራሉ።

አሁን ላይም መሰል ቅሬታወችን ለመፍታት አዲስ የካሳ ቀመር ረቂቅ አዋጅ የተዘጋጀ ሲሆን፥ አርሶ አደሮች ከመሬታቸው ሲነሱ ይያዝላቸው የነበረው የአምስት አመት ምርት አማካይ ቀርቶ በሶስት ተከታታይ አመታት ከፍተኛው ምርት ተይዞ በ10 አመት ተባዝቶ እንዲሰላ ይደረጋል።

የተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ ዋነኛ ትኩረቱን በልማት የሚነሱ ዜጎችን በዘላቂነት ማቋቋም ላይ ትኩረት አድርጎ፥ የዘላቂ ማቋቋሚያ ፈንድ እንዲቋቋም ሀሳብ አቅርቧል።

በረቂቅ አዋጁ የጓሮ አትክልት ካሳ የሚሰላበት ቀመር የተካተተ ሲሆን፥ ከዚህ ቀደም በነጠላ ተመን ዋጋ ይተመንላቸው የነበሩት አጥሮችም ቁመት፣ ወርድ እና ስፋታቸው ግምት ውስጥ እንዲገባ ይደረጋል ነው የተባለው።

ለተለያዩ የመሰረተ ልማት ገንቢዎች በጊዜያዊነት ለሚለቀቁ መሬቶች የሚከፈለው ካሳ በረቂቅ አዋጁ ቢቀመጥም በስንት አመት ተሰልቶ ይከፈል የሚለው ገና ስምምነት አልተደረሰበትም።

ከአርሶ አደሮች በጊዜያዊነት ካምፕ ተሰርቶበትም ሆነ ሲሚንቶ ሲቦካበት የቆየው መሬታችን ምርታማነቱ ቀንሷል በሚል የሚቀርበው ቅሬታም፥ በጥናት ላይ ተመስርቶ ሊፈታ እንደሚገባው አቶ ሰለሞን አንስተዋል።

የካሳ ቀመር ረቂቅ አዋጁ ከህዝብ ጋር ከተመከረበት በኋላ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እንደሚፀድቅ ይጠበቃል፤ የማስፀሚያ ደንቡም በቅርቡ ተጠናቆ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚላክ ይሆናል።

  አዲስ አበባ ፣ ህዳር 4 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ)