ዜና ዜና

የመንግስት ሰራተኞች የስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን በፍጥነት እንዲተገበር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ፡፡

የመንግስት ሰራተኞች የስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን በፍጥነት መተግበር እንዳለበት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማትና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስቴርን የ2010 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት እቅድ አፈፃፀም ገምግሟል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ማዘንጊያ አያቶ  እንዳሉት፤ የመንግስት ሰራተኞች የስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ትግበራ ዘግይቷል።

በመሆኑም "የስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ቀሪ ስራው ተጠናቆ በፍጥነት ወደ ተግበራ ማሸጋገር ይገባል" ብለዋል።

የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስትሩ አቶ ታገሰ ጫፎ የምዘናው ቀሪ ስራዎችን በቶሎ ተጠናቆ ወደ ስራ እንደሚገባ ገልጸዋል።

አቶ ታገሰ እስካሁን ባለው ሂደት ከ15 ሺህ በላይ ስራዎች ደረጃ እንደወጣላቸው ገልጸው፤ "ቀሪዎቹ አዳዲስ፣ ዓለም አቀፋዊ አደረጃጀት ያላቸውና ቅሬታ ያቀረቡ ተቋማት ናቸው" ብለዋል።

በመንግስት ተፈቅዶላቸው የመዋቅር ለውጥ የሚያደርጉ ተቋማት ከቀሪዎቹ መካከል መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ አየለች እሸቴ በበኩላቸው የ104 ተቋማት መዋቅር ጸድቆላቸው ድልድል ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።

ድልድል ያልተደረገላቸው ከአስር የማይበልጡ ተቋማት አዳዲስ  አደረጃጀትና መዋቅር ያላቸው መሆናቸውንም  ጠቁመዋል።

ክልሎች የአፈፃፀም ደረጃቸው ቢለያይም አብዛኛዎቹ ድልድሉን እስከ ወረዳ መዋቅር ማድረሳቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሶማሌ፣ ሐረሪና አፋር ክልሎች ድልድሉን ወደ ዞንና ወረዳ ለማድረስ ጅምር ላይ መሆናቸውም ተገልጿል።

ጀማሪ የዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎችን ወደ ስራ እንዲገቡ ለማስቻል  የዜሮ ዓመት የስራ ልምድ በስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ጥናቱ ላይ እንደሚካተትም ሚንስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል።

  አዲስ አበባ ህዳር 4/2010(ኢዜአ)