ዜና ዜና

የቻይና ህክምና ቡድን ለችግረኛ ተማሪዎች የህክምና ድጋፍ አደረገ፡፡

የቻይና ህክምና ቡድን አዲስ አበባ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ ችግረኛ ተማሪዎች የህክምና እርዳታ ማድረጉን  የሀገሪቱ የዜና ወኪል (ዢንዋ) ዘግቧል፡፡

የ20ኛው የቻይና ህክምና ቡድን አባላት በኢትዮጵያ ከቻይና ኤምባሲና ከሀገሪቱ ኩባንያዎች ጋር በመተባበር የምግብና የትምህር መሳሪያዎች ድጋፍ ማድረጉም በዘገባው ተመልክቷል፡፡

የህክምና ቡድኑ መሪና የልብ ሀኪሙ  ዛኦ ቼንግ እንዳሉት ነጻ የጤና አገልግሎቱ የተሰጣቸው  ሙዳይ በተሰኘው መንግስታዊ ያልሆነ ሀገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅት አጋዥነት ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ላሉ ችግረኛ ተማሪዎች ነው፡፡

 አስር አባላትን ያቀፈው የህክምና ቡድን የአፍና የመተንፈሻ አካላት ህክምናን ጨምሮ የአይን መከላከያ እርዳታና የልብ ምርመራዎችን ማድረጉንም ነው የቡድን መሪው ያብራሩት፡፡

የበጎ አድራጎት ድርጅቱ መስራችና ሃላፊ ሙዳይ ምትኩ  እንዳሉት ቤተሰቦቻቸው ችግረኞች በመሆናቸው የህክምና አገልግሎትና የትምህርት ቁሳቁስ ለማያገኙት ተማሪዎች የተደረገላቸው ድጋፍ በጣም አስፈላጊ  ነው፡፡

 በኢትዮጵያ ከቻይና ኤምባሲ ዙ ወንቂያንግን ጠቅሶ የዜና ወኪሉ እንዳስነበበው ድጋፉ የቻይና መንግሥት ለአፍሪካውያን ወዳጆቹ ያለውን ቁረጠኝነት ያሳያል፡፡

"ምንም እንኳን ቻይናም በማደግ ላይ ያለች ሀገር ብትሆንም የቻልነውን ያህል አፍሪካውያን ወዳጆቻችንን ማገዝ ግዴታችን ነው" የሚሉት ዙ ሌሎች የቻይና ኩባንያዎችም  ማህበረሰቡን የማገዝ ተግባራትን እንዲያከናውኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 ህዳር 4/2010(ኢዜአ)