ዜና ዜና

ኪራይ ሰብሳቢነትንና ብልሹ አሠራርን በመከላከል የህዝቡን ጥያቄ እንፈታለን -በድሬዳዋ አስተዳደር የኦህዴድ አመራሮች

ከኪራይ ሰብሳቢነትና ብልሹ አሰራርን በመከላከል የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውን በድሬዳዋ አስተዳደር ስር የሚገኙ የኦህዴድ አባላትና አመራሮች አስታወቁ፡፡

በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) አባላትና ደጋፊዎች ለሶስት ቀን በድርጅቱ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴና ቀጣይ አቅጣጫ ላይ ያካሄዱት ጉባኤ ዛሬ ተጠናቋል፡፡

በጉባኤው የተሳተፉ አመራሮችና አባላት ለኢዜአ እንደገለፁት የሥርዓቱ አደጋ የሆነው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባራትን በቁርጠኝነት ለመከላከል ተዘጋጅተዋል፡፡

ሥልጣንን ለግል ጥቅምና መደላደያ የሚያውሉ አንዳንድ አመራሮችን  በፅናት በመታገል ስልጣን የህዝብ መገልገያነቱ ፀንቶ እንዲዘልቅ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

በአስተዳደሩ የኡሉልሞጆ ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ ዑስማን መሐመድ በሰጡት አስተያየት የድርጅቱን አንድነት ጠብቆ የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በተደራጀ መንገድ ምላሽ ያለመስጠት ችግሮች መኖራቸው በጉባኤው  ተመልክቷል።

"ጉባኤው እያንዳንዱ አመራርና አባል ያሉበትን ክፍተቶች በጥልቀት የፈተሸበትና አምና በጥልቅ ተሃድሶው ህዝቡ ላቀረባቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የድርሻቸውን ለመወጣት አቋም ይዞ የወጣበት ነው ብለዋል ።

አቶ ዑስማን እንዳሉት በአስተዳደሩ ከጥልቅ ተሃድሶ ማግስት ጀምሮ የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት ጥረት ቢደረግም የሚፈለገው ውጤት አልመጣም፡፡

ችግሩን ለመፍታትና የወጣቱን የሥራ ጥያቄ ለመመለስ የተጀመሩ ሥራዎችን በተናበበና በተቀናጀ መንገድ ለማስኬድ ጉባኤው ምቹ ሁኔታ  መፍጠሩን የገለፁት ደግሞ አቶ ፋሚ መሐመድ ናቸው፡፡

ወይዘሪት ሰአድ መሐመድ በበኩላቸው በአንዳንድ አመራሮች የሚስተዋለውና በደማቸው ዘልቆ የገባውን ሥልጣንን ለራስ ጥቅም የማዋል ተግባር የማጥራት ጉዳይ ቀዳሚ ስራ መሆኑን በጉባኤው የጋራ ድምዳሜ የተያዘበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

"ከምን ጊዜ በላይ የተፈጠረውን አንድነትና መነቃቃት በመጠቀም ለህዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ተዘጋጅተናል" ብለዋል፡፡

የሳታፊ አባላትና አመራሮች የኦሮሞ ህዝብ አንድነቱን ጠብቆ ከሌሎች ብሔረሰቦች ጋር በመሆን በሀገሪቱ ብሎም በድሬዳዋ እየተመዘገቡ የሚገኙትን የልማት፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና የሰላም ውጤቶች እንደሚያጠናክሩ ባለዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ጉባኤያቸውን አጠናቀዋል፡፡         

 ድሬዳዋ ህዳር 3/2010(ኢዜአ)