ዜና ዜና

በደቡብ ክልል ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከገጠሩ ክፍል ሀብት የማሰባሰብ ተግባር በተሞክሮነት ሊወሰድ እንደሚገባየኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በደቡብ ክልል ከገጠሩ ክፍል ሀብት በማሰባሰብ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ ለማዋል እየተከናወነ ያለው ተግባር በመልካም ተሞክሮ ሊወሰድ እንደሚገባ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

ክልሉ ከአርሶና አርብቶ አደሩ ያሰባሰበው ድጋፍ በገጠሩ ህዝብ በግድቡ ግንባታ የራሱን አሻራ እንዲያሳርፍ ያስቻለ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ምክትል ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍቅርተ ታምር ለኢዜአ እንደገለፁት በክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ አቀባበል አስመልክቶ በተሰበሰበው ገቢ የአርሶና አርብቶ አደሮች ተሳትፎ ከፍተኛ ነው፡፡

"የክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤትና መላው አመራር የገጠሩን ህዝብ በግድቡ ግንባታ ለማሳተፍ የተከተሉት መንገድ በሌሎች ክልሎች በመልካም ተሞክሮነት ሊወሰድ ይገባል " ብለዋል ።

በገጠሩ ያለው ህዝብ ለግድቡ ግንባታ የበኩሉን ለማበርከት ከፍተኛ ፍላጎት ያለው መሆኑን የክልሉ አርሶና አርብቶ አደሮች ተሳትፎ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የደቡብ ክልል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳተፎ ምክር ቤት ዳይሬክተር አቶ ፋሲካ ጌታቸው በበኩላቸው በክልሉ ለግድቡ ግንባታ የገጠሩ ህዝብ ተሳትፎ ሊጨምር የቻለው አመራሩና የተለያዩ አደረጃጀቶች ተቀናጅተው በመስራታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከፌደራልና ክልል መገናኛ ብዙሃን በተጨማሪ የኤፍ ኤምና የማህበረሰብ ራዲዮኖችና ሚኒ ሚዲያዎች ለገጠሩ ህብረተሰብ መረጃ በማድረስ እየተጫወቱ ያለው ሚና ለተመዘገበው ውጤት አስተዋጽኦ ማድረጉንም ጠቁመዋል ።

"በክልሉ እስካሁን ዋንጫው በተዘዋወረባቸው አከባቢዎች የሚገኘው አርሶና አርብቶ አደር ከቦንድ ግዥ ውጭ 4 ሺህ 72 ሰንጋዎችና ወይፈኖች፣ 1ሺህ 960 በጎችና ፍየሎችን  በስጦታ አበርክቷል " ብለዋል ።

የከበሩ ማዕድናት ከሚመረትባቸው አከባቢዎችም ከ600 ግራም በላይ ወርቅ፣ ቡናና ሰሊጥን ጨምሮ የጥራጥሬ ሰብሎችና 90 የሚሆኑ በቅሎዎችና ፈረሶች ለግድቡ ግንባታ በድጋፍ መሰብሰባቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

የአማራ ክልል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ምክር ቤት ዳይሬክተር አቶ ላቀ ጥላዬ በበኩላቸው በገጠር ያለው ህዝብ ለግድቡ ግንባታ በዓይነትና በጉልበት የሚያበረከተውን አስተዋጽኦ ለማጠናከር ይሰራል ብለዋል።

የክልሉ አርሶ አደሮች ከቦንድ ግዢው በተጨማሪ ለስድስት ተከታታይ ዓመት በአባይ ተፋሰስ አከባቢ የተጎዳ መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በማከናወን የግድቡን በደለል የመሞላት ተጋላጭነት ለመከላከል አስተዋፆ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል ።

የኦሮሚያ ክልል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ዳይሬክተር አቶ አሚን አብዱ በበኩላቸው በክልሉ  የገጠሩን ህዝብ በስፋት በማሳተፍ ለግደቡ ግንባታ ድጋፍ የማሰባሰብ ልምድ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል ።

በጋምቤላ ክልል እየተዘዋወረ ያለው የህዳሴ ችቦ ወደ ክልሉ ሲደርስ አርሶና አርብቶ አደሩን ይበልጥ ለማሳተፍ እየተሰራ ነውም ብለዋል።

ባለፉት አራት ተከታታይ ቀናት በአርባምንጭ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ብሔራዊ ምክር ቤት ዓመታዊ ምክክር መድረክ በየክልሉ የተገኘውን ተሞክሮ በመቀመር በጋራ ለመስራት በመስማማት  ተጠናቋል፡፡

 አርባ ምንጭ ኅዳር 3/2010(ኢዜአ)