ዜና ዜና

ብአዴን ሙስና ፈጽመዋል ተብለው ጥቆማ የተደረገባቸውን አመራሮች በማጣራት ተጠያቂ እያደረገ ነው

የብሔር አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) በጥልቅ ተህድሶ ሙስና ፈጽመዋል ተብለው ጥቆማ የተደረገባቸውን 857 መካከለኛና ከፍተኛ አመራሮች በማጣራት ተጠያቂ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።

የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለምነው መኮንን የሕዳር 11 በዓል አከባበርን አስመልክተው ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳሉት፣ ብአዴን አመራሩ የተሰለፈበትን ዓላማ የመሳት ችግር አጋጥሞት ነበር።

በተለይ ከሙስናና ብልሹ አሰራር ጋር በተያያዘ ሕዝቡ በመሪዎቹ ላይ ከባድ ጥርጣሬ አሳድሮ ስለነበር ብአዴን ችግሩን ለማጣራት ሰፊ ሥራ ሰርቷል።

አመራሩን ፊት ለፊት ከመገምገምና ከማስተካከል በተጨማሪ ከድርጅቱ የአሰራር መርህ ውጭ የእውነት አፈላላጊ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በልዩ ሁኔታ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

ግብረ ኃይሉ በየአካባቢው በተቀመጡ የሃሳብ መስጫ ሳጥኖችና በአካል የደረሱትን 857 ጥቆማዎችን የማጣራትና እውነቱን የማግኘት ሥራ መሰራቱንም አቶ አለምነው አመልክተዋል።

በእዚህም ከቀረቡት ጥቆማዎች ውስጥ 117 የሚሆኑ ከፍተኛ አመራሮች ሆነው መገኘታቸውን ገልጸው፣ ከእነዚህ ውስጥ 42 በመቶ የሚሆኑት መሬት ያለአግባብ በመውሰድ፣ ከግብር ስወራና በዝምድና ከመቅጠር ጋር በተያያዘ ችግር ውስጥ መግባታቸው ተረጋግጧል።

ጥቆማ ከደረሰባቸው 740 መካከለኛ አመራሮችም 355ቱ መሬትን ደራርበው በመውስድና በመሰል ችግሮች ጥፋተኛ ሆነው መገኘታቸውን አስታውቀዋል።

በሙስና ችግር ውስጥ የተገኙትን ከኃላፊነት ቦታቸው የማንሳትና ዝቅ ብለው እንዲመደቡ እንዲሁም በሙስና ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በህግ እንዲታይ በመደረግ ላይ መሆኑን አብራርተዋል።

እንደ አቶ አለምነው ገለጻ፣ ብአዴን ከህዝባዊነቱ ላለመለየት ችግሮቹን በጥልቅ ታህድሶ በመገምገም የማስተካከል ሥራ እየሰራ ነው።

ከጥልቅ ተሀድሶ በኋላ በተከናወኑ ተግባራት የአመራሩን የተዛባ አመለካከት በማስተካከል የአስተሳሰብ ግልጽነትና የህዝብ አገልጋይነት መንፈስ እየዳበረ መምጣት ከተገኙ ውጤቶች ቀዳሚ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ ከህዝብ ጥቅም ጎን በመቆም ፊት ለፊት የመታገልና የማስተካከል ልምድ መገኘቱንና የህዝብ ጥረትን የሚደግፍ አመራር ማግኘት እየተቻለ ነው።

አቶ አለምነው እንዳሉት፣ የሕዝብ አንገብጋቢ ችግር ለይቶ መፍታት፣ ህዝባዊ አንድነትን መገንባት፣ ዴሞክራሲያዊ ግንኙነትን ማዳበርና መሰል ለውጦች ከጥልቅ ታህድሶ በኋላ በድርጅቱ የመጡ ለውጦች ናቸው።

በርካታ የሚቀሩና በሂደት ላይ ያሉ ጉዳዮች እንዳሉም ጠቁመዋል።

በቀጣይ የተጀመሩ ለውጦችን በመያዝ ከህዝቡጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ በመታገል የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት በልዩ ትኩረት እንደሚሰራም አቶ አለምነው አስታውቀዋል።

"የብአዴን ህዝባዊነትና የአላማ ፅናት ለዴሞክራሲያዊ አንድነት" በሚል መሪ ቃል የድርጅቱን 37 ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

ህዳር 2/2010 /ኢዜአ/